
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዐቢይ ጾም የመጨረሻው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ውስጥ ካሉት ቀናት አራተኛው ዕለት ጸሎተ ሐሙስ ይባላል። በዚህ ዕለት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች በየዓመቱ ታላላቆች በታናናሾች እግር ሥር ወድቀው እንደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግር የማጠብ ሥርዓትን ያከናውናሉ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ጎጃም ሀገረ ሥብከት የባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት ሥብከተ ወንጌል እና ልማት ክፍል ተጠሪ መምህር ሰናይ አሞኘ እንዳሉት ጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ዝቅ ብሎ እግራቸውን ያጠበበት፣ ትህትናን ያስተማረበት ቀን ነው፡፡
በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 13 ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሐሙስ ወገቡን ታጥቆ ደቀ መዛሙርቱን እግራቸውን እንዳጠበ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም የተጎሳቆለውን ዓለም ከሀጢአት ባርነት ነጻ ለማውጣት ትህትናን ያሳየበት መኾኑንም ነው ያነሱት።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባሳየው ትህትና ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ መምህሬ ኾነህ እንዴት እኔን ታጥበኛለህ አለው፡፡ ክርስቶስም እኔ አንተን ካላጠብኩ የመንግሥት ሰማያት ባለቤት አትኾንም አለው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ሁሉንተናውን ለመታጠብ ፈለገ፡፡ ክርስቶስም አንዱ አካል ከታጠበ ሁሉም ንጹህ እንደኾነ ነገረው፡፡ እግዚአብሔርም ወገቡን አደግድጎ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጀምሮ ሁሉንም አጠባቸው” ብለዋል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀመዛሙርቱን እግር ዝቅ ብሎ አጥቦ ትህትናን እንዳስተማረ ሁሉ አሁንም ድረስ በተዋረድ የሚገኙ አባቶች እንደየማዕረጋቸው ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ባለው ቅዳሴ መግቢያ እጽበተ እግር/እግር ማጠብ/ እንደሚያከናውኑ መምህሩ ነግረውናል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ትህትናን እንዳስተማረ ሁሉ ሰዎችም በትህትና ዝቅ ብለው ታናናሾችን እንዲመለከቱ፣ የተቸገሩትን እንዲጠይቁ እና እርስ በእርስ በመረዳዳት እንዲኖሩ ጠይቀዋል። “ብዙ ፍሬ የያዘ ዛፍ የሚታወቀው ራሱን ዘንበል በማድረጉ ነው እና ሰዎች ባወቁ ቁጥር ትህትናን ይላበሳሉ፤ ዝቅ ብለውም ያገለግላሉ” ብለዋል። አንዱ ለአንዱ ትሁት በመኾን ሰላም የሰፈነበት አካባቢ መፍጠር እንደሚገባ የገለጹት መምህሩ ትህትናን ገንዘብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
እብሪት እና ትዕቢት ውርደት እና ውድቀት እንደሚያመጣ ኹሉ ትህትና ክብረትን ስለሚያመጣ ሁሌው የክርስቶስን አርዓያ መከተል፣ መርሕ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል። እርስ በእርስ መዋደድ እና መፈቃቀር ይገባል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!