በዓላት በሰላም እንዲከበሩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ገለጸ።

18

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የስቅለት እና የፋሲካ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ለማስቻል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ፖሊስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ መላው የጸጥታ አካላቱን ያሳተፈ ውይይት ተከናውኗል፡በመድረኩ ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታን እና መደበኛ የወንጀል መከላከል የተግባር አፈጻጸሞች ላይ ትኩረት ያደረገ ገለጻ ተደርጓል።

ከበዓላቱ መከበር ጋር ተያያዞ በከተማው ላይ እንደ ስጋት የሚታዩ ችግሮችን አስቀድሞ በመለየት በቀጣይ መከናወን በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፈንታ በጽንፈኛ ቡድኖች ላይ እየተወሰደ ከሚገኘው ጠንካራ እርምጃ ጎን ለጎን የስቅለት እና የፋሲካ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ የጸጥታ አካላት ቅንጅታቸውን በማጠናከር የክፍለ ከተሞቻቸውን ተጨባጭ እና ነባራዊን ሁኔታ ያገናዘበ ጸጥታን የማረጋገጥ ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ከስቅለቱ ጀምሮ የፋሲካ በዓልን ተከትሎ በሚመጡ የበዓል ሰሞን ሊኖር የሚችለው የሰው እና የተሸከርካሪን እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረገ የወንጀል እና የትራፊክ አደጋ ቅድመ መከላከል ተግባር ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መላኩ ፈንታ አስታውቀዋል ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው በዓሉ በየቤቱ የሚከብር እንደመሆኑ መጠን እንቅስቃሴዎች ከበዓል በፊት ባሉ ቀናት እንደሚበዙ ጠቁመው በባዛሮች፤ በገበያ ቦታዎች ላይ በሚስተዋሉ የበዓል ግብዓቶች ላይ ሰው ሠራሽ የግብዓት እጥረት እና የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ የከተማ አሥተዳደሩ ባቋቋመው ግብረ ኅይል ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በንግድ ሥርዓቱ ላይ ሕገ-ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ተግባር በማገዝ ኅብረተሰቡ መረጃ በመስጠት ሊተባበር ይገባል ብለዋል፡፡ የምርት አቅርቦት ላይ እና የቁም ከብት ገበያ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር የሚያደርጉ ሕገ-ወጥ ደላሎች ላይ ተገቢው ክትትል በማድረግ መቆጣጠር እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ባልተፈቀዱ ቦታዎች ላይ የሚደረግ ግብይትን መቆጣጠር ትኩረት እንደሚሰጠው ያብራሩት ኅላፊዋ ለትራፊክ ስጋት የሆነውን የጎዳና ላይ ንግድን ጨምሮ የስርቆት ወንጀል፤ ሐሰተኛ የብር ኖት ዝውውር፤ በምግብ ውስጥ ባዕድ ነገር ቀላቅለው በሚሸጡ አካላት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ሊዲያ ግርማ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በዚህ ዓመት በርካታ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት በሰላም መከበራቸውን አስታውሰው የስቅለት እና የፋሲካ በዓላት በተመሳሳይ የጸጥታ ሁኔታ በሰላም እንዲያልፍ ቀደም ሲል የታዩ መልካም ተሞክሮዎችን በመቀመር ጥናት ላይ ያተኮረ የስምሪት አቅጣጫ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ከወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ አኳያ በከተማው ዋና ዋና የገበያ ቦታዎች ፤ በመዝናኛ አካባቢዎች፤ በቤተ እምነቶች እና በጥናት በተለዩ አካባቢዎች ላይ ጠንካራ የጥበቃ ተግባር እንደሚከናወን አብራርተዋል፡፡ በተለይም የሃይማኖቱ ተከታዮች በምሽት ወደ ቤተ እምነቶቹ ለአምልኮት ሲሄድ ምንም አይነት ስጋት እንዳይፈጠር ጠንካራ የጥበቃ ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት። ኅብረተሰቡም ለሰላሙ ስጋት የሆኑ ነገሮች ሲያጋጥሙት ለጸጥታ አካላት ተገቢውን መረጃ በመስጠት ተባባሪ መሆን እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

ለመላው የክርስትና ዕምነት ተከታዮች በዓላቱ የጤና፣ የፍቅር እና የመተሳሰብ እንዲሆን የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ መልካም ምኞት ማስተላለፉን ኢፕድ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አቀባበል እየተደረገ ነው፡፡
Next article“እብሪት እና ትዕቢት ውርደት እና ውድቀት፣ ትህትና ደግሞ ክብረትን ያስገኛል” መምህር ሰናይ አሞኘ