ተስፋ ነዳያን የበጎ አድራጎት ማኅበር ለ400 አቅመ ደካሞች የበዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ።

15

ከሚሴ: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተስፋ ነዳያን የበጎ አድራጎት ማኅበር የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥ ለሚኖሩ 400 አቅመ ደካሞች የበዓል መዋያ ድጋፍ አድርጓል። የማኅበሩ አሥተባባሪ ወጣት ኤርሚያስ ተፈራ እንደገለጸው ከተቋቋመ አሥር ዓመታትን ያሥቆጠረው ማኅበር ኀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ በመጠቀም ከ600 ሺህ ብር በላይ በማሰባሰብ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።

የተስፋ ነዳያን የበጎ አድራጎት ማኅበር ሥራ አሥፈጻሚ ወጣት ብስራት ዮሀንስ ማኅበሩ ከዚህ ቀደም ለዒድ አልፈጥር በዓል መዋያ ድጋፍ ማድረጉን ገልጻለች። ማኅበሩ በርካታ አባላትን ያፈራ ጠንካራ የበጎ አድራጎት ማኅበር መኾኑንም ጠቁማለች፡፡

አሁን ላይ ለ400 አቅመ ደካሞች ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሺህ ብር ቤት ለቤት በመሄድ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጻለች። ከዚህ በፊትም ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን ለመወጣት ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጻለች።

ድጋፉ የተደረገላቸው አካላት ለበጎ ሥራው አመስግነው መደሰታቸውንም ገልጸዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከሲሚንቶ ጋር ተጭኖ ወደ ከሚሴ ከተማ ሊገባ የነበረ የነፍስ ወከፍና የቡድን የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ስር ዋለ።
Next articleለሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን አቀባበል እየተደረገ ነው፡፡