
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መነሻውን ከመቀሌ በማድረግ ከሲሚንቶ ጋር ተጭኖ ወደ አማራ ክልል ከሚሴ ከተማ ሊገባ የነበረው የነፍስ ወከፍ እና የቡድን የጦር መሣሪያ በሠራዊቱ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
በሰሌዳ ቁጥር አማ 17744 ኤፍ ኤስ አር ተሽከርካሪ በድብቅ የተጫነው ሕገ ወጥ የቡድን እና የነፍስ ወከፍ የጦር መሣሪያ በኅብረተሰቡ ጥቆማ ደጋን ከተማ ላይ ከነአሽከርካሪው እና ረዳቱ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው፡፡
በሰሜን ምሥራቅ ዕዝ የሻለቃ አመራር ሻምበል ውበቱ ስማቸው የጦር መሣሪያው የተያዘው ሕዝቡ በሰጠው መረጃ መኾኑን ገልጸው ሲሚንቶ በጫነ ተቆራጭ ተሳቢ በመደበቅ ለጠላት ለማድረስ የታቀደ እንደነበር ተናግረዋል።
የተያዘው የጦር መሳሪያ ሁለት ዲሽቃ፣ አንድ ስናይፐር አንድ አርባ ጎራሽ እና አራት ኤስ ኬ ኤስ በድምሩ ስምንት ነው። የጦር መሣሪያውን ለአሸባሪው ሸኔ ለማድረስ ታስቦ የነበረ ቢኾንም ኅብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ ከታሠበው ሳይደርስ ደጋን ከተማ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን በሚያይ እና በሚሰማ ጊዜ መረጃውን ያለምንም ፍራቻ ለሠራዊቱ በማድረስ ሰላምን ማስቀጠል እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!