ሜይ ዴይ-የዓለም ሠራተኞች ቀን

56

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መነሻው በነጻ ገበያ ሥርዓት ስም ካፖታሊዝምን በምታራምደው አሜሪካ ነው፡፡ ግንቦት 1886 ዓ.ም በችካጎ ከተማ የሄይማርኬት ሠራተኞች የመብት ትግል መቀስቀሱ፣ ከ400 ሺህ በላይ ሠራተኞች የስምንት ሰዓት የሥራ ጊዜ በመጠየቅ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ይነገራል፡፡ በተፈጠረው ግጭት ጉዳት፣ እሥራት እና ሞት ቢከሰትም ከዚያ በኋላ ግን የሄይማርሄት ጉዳይ አይረሴ ኾነ፡፡

የዓለም ሠራተኞች በነጮቹ ግንቦት አንድ እንዲከበር ውሳኔ ላይ የተደረሰው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1889 በዓለም አቀፍ የሶሻሊስት ቡድን እና በሠራተኞች ማኅበራት ውሳኔ ሲኾን በ1886 ዓ.ም በችካጎ የተቀሰቀሰው የሄይማርኬት የሠራተኞች የመብት ጥያቄ አድማን ለማስታወስ በማሰብ ነው፡፡ የአሜሪካ መንግሥትም ሲብላላ የቆየውን የሠራተኞች ጥያቄ ለመዘከር ግንቦት 1 ቀን የሠራተኞች ቀን ኾኖ እንዲከበር አጸደቀ፡፡

ሶቪዬት ህብረት መራሹ የምሥራቁ ጎራ በዓሉን በድምቀት ያከብረው እና እታገልለታለሁ የሚለውን የሠራተኛው መደብ ያነሳሳበትም ነበር፡፡ ከዚያ ባለፈም ሜይ ዴይ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሠራተኞች መሠረታዊ መብቶችን መከበር አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይነገርለታል፡፡

ከ1991 ዓ.ም የሶቪየት ሕብረት መበታተን እና ዓለም ወደ ምዕራባውያኑ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሃብት ጎራ ከተመለሰች በኋላ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) የቀድሞ ግርማ ሞገሱን አጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም በ160 ሀገራት ይከበራል፡፡ ሀገራት ቀኑን በሕግ አጽድቀው ቢያከብሩትም የሠራተኞች መብት ግን ሙሉ በሙሉ እንዳልተከበረ ይነገራል፡፡

በወቅቱ “በሠራተኛው እና በከበርቴው መካከል ያለው ቅራኔ እየተካረረ ሲሄድ ሠራተኛው የባርነት ቀንበሩን ጥሎ የራሱን ነጻ መንግሥት ማወጁ አይቀርም” በሚል ጽኑ እምነት የሠራተኛው መደብ አመጽን ጨምሮ በተለያዩ አማራጮች መብቱን እና ጥቅሙን እንዲያስከብር የመከረው እና የመራው ካርል ማርክስ በብዙው ይጠቀሳል፡፡

በሠራተኛው እና በከበርቴው መካከል የ“መደብ” ልዩነት እንዳለና የከበርቴውን ሥርዓት በትግል አስወግዶ ኮሙኒዝም የሚባል የማኅበረሰብ ክፍል ለማይኖርበት ሥርዓት መመሥረት ሁለንተናዊ ትግል ለማድረግ እንደ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ያሉ ማታገያ መድረኮችን አበረታትቷል፡፡
ከፍተኛ የሠራተኞች ተጋድሎ የተካሄደባት አሜሪካ የሠራተኛው ትግል በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ከታሪክ እንዲጠፋ ጥረት ብታደርግም አልቻለችምና ቀኑን አስባው ትውላለች፡፡ 66 ሀገራት ብሔራዊ በዓል ሲያደርጉት ሌሎቹ ደግሞ አስበውት ይውላሉ፡፡

በባሕል እና በታሪክ ኅብረተሰባዊነት የሚያጠላባቸው ኢትዮጵያውያንም እንደ ቀድሞው በወታደራዊ ማርሽ እና በፖለቲካ ድምቀት ባይታጀብም የሠራተኞች ቀን ታስቦ ይውላል፡፡ ያም ኾኖ ለሠራተኞች መብት እና ጥቅም መከበር እየሠራ መኾኑን እና ፍትኃዊ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት እንዲኖር፣ የሠራተኛው መብት እንዲከበር ለሚታገለው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) እንደ ትግል ምልክት ኾኖ ያገለግላል፡፡

ኢሠማኮ የሰሜን ምዕራብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አግማስ ዳኘው ኮንፌዴሬሽኑ የሠራተኞችን መብት እና ጥቅም ለማስከበር አሁንም እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ ስለኾነ በዚያው ልክ የሠራተኞችም ቁጥር ቢጨምርም አደረጃጀቶች ኖረውና ጠንክረው ጥቅማቸውን በማስከበር በኩል ግን ውጤቱ አናሳ መኾኑን ነው ያስረዱት።

ከንጉሱ ዘመን አወጅ 49/1954 ጀምሮ እስከ የአሁኑ 1156/2011 ድረስ በርካታ የአሠሪ እና ሠራተኛ ድንጋጌዎች ቢኖሩም የሠራተኛው መብት አልጋ በአልጋ አይደለም። በወጣው ሕግ ልክ በርካታ ሠራተኞች መብታቸውን እየተጠቀሙበት አለመኾኑን አክለዋል። ለዚህም ዋናው ምክንያት አለመደራጀታቸው ነው ብለዋል።

በ1948 ዓ.ም የወጣው ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድንጋጌ የሥምምነት ቁጥር 87 ተቀጣሪ ሠራተኞች መደራጀት እና መብት እና ጥቅሞቻቸው ላይ መደራደር እንደሚችሉም መደንገጉን እና የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ድንጋጌውን ተቀብሎ እንዳጸደቀው ነው አቶ አግማስ የገለጹት።

አቶ አግማስ የፋብሪካ ባለቤቶች ሠራተኞች እንዳይደራጁ መከልከል፣ ማባረር፣ ማዛወር፣ ማሳደድ እና ማኅበሩን የማፍረስ ሥራዎችን በመሥራት የሠራተኛውን ጉልበት ለመበዝበዝ የሚደረጉ ፍላጎቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። የፋብሪካ ሠራተኞች ከሥራቸው የመባረር እና ለችግር የመዳረግ አጋጣሚዎች ሰፊ መኾናቸውን ጠቅሰው በሠራተኛ ማኅበር ከታቀፉት ግን የተባረረ እንደሌለ ጠቅሰዋል።

በየፋብሪካዎች መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር መኖር እንዳለበት ሕጉ ቢፈቅድም በአሠሪዎች አለመፍቀድ ምክንያት ከተደራጀው ይልቅ ያልተደራጀው እንደሚበዛ ተናግረዋል። በሰሜን ምዕራብ ቀጣና 190 ማኅበራት መኖራቸውን ጠቅሰው ፋብሪካዎች በየጊዜው ስለሚቋቋሙ የሠራተኛ ማኅበር የሌላቸው ቁጥር እንደማይታወቅ ነው የገለጹት።

በአማራ ክልል የፍትሕ አካላት በሠራተኞች ጉዳይ የውሳኔ መዘግየት የሠራተኛውን ችግር እንዳከፋው እና የሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ተቋም ፈርሶ በሥራ ሂደት ደረጃ ብቻ መወሰኑ ተጨማሪ ችግር መኾኑን አቶ አግማስ አመላክተዋል።

የአሠሪ እና ሠራተኛ የኅብረት ሥምምነቶች የጥቅም እና የመብት ጉዳይ በመደራደር እንዲሠራ እንደሚደረግ የጠቀሱት አቶ አግማስ የሠራተኞች አነስተኛው የክፍያ መጠን ወለል እንዲወሰን፣ የሥራ ግብር እንዲቀነስ፣ የመደራጀት መብት እንዲከበር አሁንም ጥያቄ እያቀረብን ነው ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራተኞች ቀንን አከበረ።
Next articleከሲሚንቶ ጋር ተጭኖ ወደ ከሚሴ ከተማ ሊገባ የነበረ የነፍስ ወከፍና የቡድን የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ስር ዋለ።