
ደብረ ማርቆስ: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የእንስሳት ልማት ዘርፉን በዘመናዊ አሠራር በመደገፍ እየጨመረ የመጣዉን የማኅበረሰቡን የእንስሳት ተዋጽዖ ፍላጎት የሚያሟላ አቅርቦት እንዲኖር እየሠራ መኾኑን የዞኑ እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ለመጭው የትንሣኤ በዓልም ከ800 ሺህ በላይ የቁም እንስሳት ደልበዉ ለገበያ እንደሚቀርቡም ተገልጿል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን 6 ሚሊዮን የሚጠጋ የቁም እንስሳት እንደሚገኝ ከተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ የተገኘዉ መረጃ ያመላክታል፡፡ ይህንን ከፍተኛ ቁጥር ያለዉን የእንስሳት ሃብት አሠራርን በማዘመን ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ አቶ ጥላሁን ንጋቱ ገልጸዋል፡፡
የእንስሳት ልማት ዘርፉን በዘመናዊ አሠራር በመደገፍ በተለይም በበዓላት ወቅት እየጨመረ የመጣዉን የእንስሳት ተዋጽዖ ፍላጎት ሊመጥን የሚችል አቅርቦት እንዲኖር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችና ወጣቶች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገቡ መኾኑንም ኀላፊው ጠቁመዋል።
አቶ ጥላሁን የዞኑ ማኅበረሰብ እንስሳትን የማርባትና የማድለብ ልምድ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል። ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ የእንስሳትን ዝርያ በማሻሻል እና ጤናቸዉን በመጠበቅ የወተት እና የሥጋ ምርትን ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
የተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ በበዓላት ወቅት በቆዳና ሌጦ ምርቶች ላይ የሚስተዋለው ብክነት እንዲቀንስ በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በዞኑ በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት ተስተጓጉሎ የቆየውን የእንስሳት ሕክምና እና የመድኃኒት አቅርቦት እንደገና ተደራሽ ለማድረግ ተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ በትኩረት እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ:- ወንድወሰን ዋለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!