
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪው አብዮት የተስፋፋበት ወቅት ነበር። ለዓመታት የቆየው የእርስ በእርስ ጦርነት ማብቂያ ላይ የነበረችው አሜሪካ ከእርሻ ወደ ኢንዱስትሪ የተሸጋገረችበት ወቅትም ነበር። የኢንዱስትሪ መስፋፋቱ ለበርካታ አሜሪካውያን በሥራ ላይ እንዲሰማሩ መልካም አጋጣሚ ፈጠረ።
መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት በቀን እስከ 16 ሰዓታት ያለ እረፍት መሥራት ጀመሩ። እስከ አምስት ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ ህጻናት ጭምር ከባድ የጉልበት ሥራዎችን በሰዓት እስከ 20 ሳንቲም እየተከፈላቸው ይሰሩም ነበር። በአሜሪካ የኢንዱስትሪውን ማበብ ተከትሎ ኑሯቸውን ለማሻሻል ከሚፈልጉ የአሜሪካ ዜጎች ባሻገር ስደተኞች በተለይም አውሮፓውያን ወደ አሜሪካ እንዲሰደዱ ምክንያት ኾነ።
የኢንዱስትሪ መስፋፋቱ የሥራ እድል ይዞ ቢመጣም ምቹ ባልኾነ የሥራ ቦታ እና በዝቅተኛ ክፍያ ምክንያት ሠራተኞች ለሕይዎት ማጣት፣ ለአካል መጉደል፣ ለዘላቂ የጤና ችግር እየተጋለጡ መጡ። እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት ከ1860ዎቹ ጀምሮ ሠራተኞች የሥራ ሰዓት በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ ኾኖ የሙሉ ቀን ደመወዝ እንዲከፈላቸው ባልተደራጀ መልኩ መጠየቅ ጀመሩ። ይሁን እንጅ የሠራተኛውን ጉልበት በመበዝበዝ ከፍተኛ ትርፍ ማጋበስ የለመዱ የዘመኑ ጉምቱ ከበርቴዎች ለጥያቄው ምላሽ መስጠት አልፈለጉም።
ይኽ ሰሚ ያጣው ጥያቄ ሠራተኞች እንዲደራጁ እና ከፍተኛ ተጋድሎ እንዲያደርጉ በር ከፈተ። ጥያቄውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገፋ ሄደ። ይህን ተከትሎ ሠራተኞችም “አድማ አስነስታችኋል፤ ምርታማነት እንዲቀንስ አድርጋችኋል፤ በምንፈልገው መጠን ካልሠራችሁ አንፈልጋችሁም” እየተባሉ ከሥራ ተሰናበቱ።
የዩናይትድ ስቴትስ እና የካናዳ የንግድ እና የሠራተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ሠራተኞች ከግንቦት 1/1886 ጀምሮ በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ እንዲሠሩ ጥያቄውን ማቅረብ ቀጠሉ።
በቀረበው ጥያቄ አሠሪዎች አለመሥማማታቸውን ተከትሎ በቺካጎ የሚገኙ ሠራተኞች የስምንት ሰዓት ሥራ እንዲከበር ሰልፍ ወጡ። ሰልፉን ተከትሎ በፖሊሶች በተወሰደ እርምጃ የሰዎች ህይዎት አለፈ። በዩናይትድ ስቴትስ ችካጎ የተነሳውን የሠራተኞች ንቅናቄ ተከትሎ በአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ ሠራተኞችም ደግፉት።
ዓለም ዓቀፉ የሶሻሊስት ፓርቲዎች ምክር ቤትም በፈረንጆቹ አቆጣጠር ግንቦት 1/1889 ፓሪስ ውስጥ ኮንፈረንስ አካሄደ። በኮንፍረንሱ የሥራ ሰዓት ስምንት ሰዓት እንዲኾን የቀረበውን ሃሳብ ለመደገፍ ግንቦት 1/1890 በመላው ዓለም ትዕይንተ ሕዝብ እንዲደረገ አዋጅ አወጣ። በ1894 የሶሻሊስት ዲሞክራቲክ ፓርቲ ድርጅቶች እና የንግድ ማኅበራት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአምስተርዳም ኮንፍረንስ አካሄዱ። በኮንፈረንሱ ግንቦት አንድ ላብ አደሮች ከሥራ ነጻ እንዲኾኑ እና የሥራ ሰዓትም ስምንት ሰዓት መኾኑን ሕጋዊ እውቅና አገኘ።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ በርካታ ሀገሮች በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሚያዚያ 23 በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ደግሞ ግንቦት አንድ ቀን የላብ አደሮች ቀን ወይም ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን እየተባለ ለሠራተኞች መብት ህይዎት የከፈሉ ሰዎች የሚታሰቡበት ቀን እንዲኾን ተደርጓል። በኢትዮጵያም ከአራት አስር ዓመታት በላይ ቀኑ ታስቦ ውሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!