የሰራተኞች ቀን መከበር ለኢትዮጵያ እና ለመላው ዓለም ምን ጥቅም አስገኘ?

24

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ላይ ሰላማዊ ሰልፎችን እና ትዕይንተ ሕዝብ ማድረግ የተጀመረው ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ነበር። ለሰልፉ ጅማሮ ምክንያቱ ደግሞ በኢንዱስትሪ አብዮት ወቅት የፋብሪካ ባለቤቶች ሠራተኞቻቸው ከእሑድ በስተቀር በየቀኑ 16 ሰዓት እንዲሠሩ በማድረጋቸው በሰራተኞች ላይ ከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛ ያደርስ ስለነበር ነው።

ይኽን ተከትሎ የአሜሪካ እና የካናዳ የንግድና የሠራተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ሠራተኞች በቀን ስምንት ሰዓት ብቻ እንዲሠሩ ጥያቄ አቀረቡ። አሠሪዎች ግን በጥያቄው ባለመስማማታቸው ግንቦት አንድ ቀን 1886 ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ። በዩናይትድ ስቴትስ ቺካጎ ኢሊኖይ ውስጥ በሄይማርኬት ዓደባባይ የሠራተኞችን ንቅናቄ በመደገፋቸው በርካታ ሰዎች ሕይዎታቸውን አጡ፡፡

በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ በኾላንድ፣ በጣልያን፣ በሩሲያ እና በስፔን የሚገኙ ሠራተኞችም ንቅናቄውን ደገፉት፡፡ የኾነ ኾኖ የዓለም ሶሻሊስት ፓርቲዎች ምክር ቤት በ1889 ፓሪስ ውስጥ ባደረገው ስብሰባ የሥራ ሰዓት ስምንት ሰዓት ብቻ እንዲኾን የቀረበውን ሐሳብ ለመደገፍ ግንቦት 1 ቀን 1890 በመላው ዓለም ትዕይንተ ሕዝብ እንዲደረግ አዋጅ አወጣ።

ከዚያ ጊዜ አንስቶ ግንቦት 1 ሠራተኞች ተስማሚ የሥራ ኹኔታ እንዲፈጠርላቸው ለመጠየቅ ሰልፍ የሚወጡበት ዓመታዊ በዓል ኾነ። በመኾኑም በበርካታ ሀገሮች ግንቦት 1 ቀን 1886 ጀምሮ በዓሉ እየተከበረ ይገኛል፤ የሠራተኞች ቀን! በተለይ አፍሪካውያን ሠራተኞች ቀኑን በማክበራቸው ምን አገኙ? ትውልዱስ ምን ተማረበት? በሚሉት እርሰ ጉዳይ ዙሪያ የታሪክ መምህር ሙላት ዳኘውን አነጋግረን የሰጡንን ምላሽ እንካችሁ ብለናል፡፡

ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ቀን የሚከብረው ለሠራተኞች መብት እና ጥቅም መከበር ሲታገሉ መስዋዕትነት የከፈሉ ሠራተኞችን ለመዘከር እና ትውልዱን ለቀጣይ የመብት ትግል ለማስነሳት ነው ይላሉ መምህሩ ፡፡ በዓሉ በኢትዮጵያ በደርግ ስርዓት “የሠራተኞች ቀን” በሚል ይከበር ነበር፡፡ “ሆድ ሲያውቅ” በሚል ብሂል ሠራተኞች የኾዳቸውን በኾዳቸው ይዘው “ሶሻሊዝም ይለምልም! ከቆራጡ መሪያችን ጋር ወደፊት! ደመወዝ ይጨመረን! የሥራ ደህንነት ይከበርልን!…የኑሮ ውድነቱን መንግሥት ያረጋጋልን! ” የሚሉ መፈክሮችን በማሰማት ያከብሩት ነበር ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

ሠራተኞች ጠንከር ያሉ ጥያቄአቸውን እንዳያቀርቡ አፈናው እና ግድያው ቢያስፈራቸው ውጭ ሀገር በሚገኙ ሬዲዮ ጣቢያዎች ለአብነት በአሜሪካ እና በጀርመን ድምጽ አማካኝነት ያሰሙ ነበር ይላሉ መምህሩ፡፡ ይኽ የሠራተኞች ቀን ኢሕአዴግ ስልጣን ሲይዝ ስያሜው” የላብ አደሮች ቀን ” በሚል መቀየሩን መምህሩ አስታውሰዋል፡፡ በሀገሪቱም የሕትመት እና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በመበራከታቸው ሠራተኞች በዓሉን አስታከው “ደመወዝ ይጨመረን! የሥራ ሰዓት ስተካከልልን!” በሚል የሚያስተጋቡትን ጥያቄ የግል የመገናኛ አውታሮች እስከ ዓለም የሥራ ድርጅት አደረሱት ነው ያሉት፡፡

መንግሥትም ሰራተኛው ሜይ ዴይን አሳቦ የሚያቀርበው ጥያቄ እንደ ሺል መግፋቱን ተገነዘበ፡፡ በመኾኑም ለአንድ የጽዳት ወይም የጥበቃ አልያም የአትክልት ሠራተኛ በወር የሚከፈለውን 55 ብር ደመወዝ ወደ 127 ብር አሳደገው ብለዋል፡፡ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የመንግሥት ሠራተኞች ዓርብ ቀን በቤተ እምነታቸው ተገኝተው እንዲጸልዩም የሰዓት ሽግሽግ የተደረገላቸው የሠራተኞች መብት ጥያቄ ውጤት ነው ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ስንወጣ ዚምባብዌን እናገኛለን። በዚምባብዌ የመንግሥት እና የግል ድርጅት ሠራተኞች በእንግሊዛውያን አሠሪዎቻቸው የሚከፈላቸው ምንዳ ዝቅተኛ በመኾኑ በየጊዜው ሁከት እና ብጥብጥ ያስነሱ ነበር፡፡ ሜይ ዴይን ሲያከብሩ ደግሞ “ነጮች ሀገራችንን ለቅቀው ይውጡ! ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ! ” የሚሉ መፈክሮችን አንግበው ለዓለም መንግሥት ጥሪ ያሰሙበት ነበር፡፡

በዚምባብዌ አንድ እንግሊዛዊ እና ዚምባብዌያዊ በተመሳሳይ ሰዓት ተመሳሳይ ሥራ ሠርተው የሚከፈላቸው ደመወዝ የተለያየ መኾን እንደሌለበት በሰልፍ የሚገልጹት የሜይ ዴይ ዕለት ነበር፡፡ ጥያቄአቸውንም ከዓመት ዓመት አጠናክረው በማቅረባቸውም በርከት ያሉ እንግሊዛውያን ዚምባብዌን ለቅቀው ወጡ፡፡ በዚምባብዌ ኢንዱስትሪዎች ዚምባብዌያውያን ብቻ እንዲሰሩባቸው ተደረገ፡፡ ለዕኩል ሥራም ዕኩል ክፍያ ታወጀ ብለዋል፡፡

የኾነ ኾኖ ዚምባብዌ አሁን ድረስ ከነጮች ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ባለመላቀቋ ሠራተኞች እስከ 2023 ድረስ ተደራጅተው መብታቸውን ለማስከበር ሜይዴይን በመሣሪያነት እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ መምህሩ ጠቁመዋል፡፡ በሩዋንዳ ፖል ካጋሜ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በሠራተኞች ቀን የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በፍጥነት እየተሰጣቸው ይገኛል ያሚሉት የታሪክ መምህር ሙላት የመንግሥት ሠራተኞች የመደራጀት እና የመደራደር መብታቸው ተከብሯል ብለዋል፡፡ የሠራተኞች የሙያ ደህንነት መጠበቂያ ፖሊሲ ወጥቶ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

በሩዋንዳ የብሔር ቡድንተኝነት መክኗል፤ ሁሉም ሠው ሩዋንዳዊ ነው፡፡ ሩዋንዳውያን ያሳለፉትን የዘር ፍጅት “አንረሳውም! ግን አንደግመውም!” የሚል መሪ ሃሳብን አንግበው በሠራተኞች ቀን ሠራተኞችን ለልማት የሚያተጉ ድምጾችን በማሰማት እንደሚያከብሩት የታሪክ ምሁሩ አስታወሰዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካም ነጮች እና ጥቁሮች ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ አያገኙም ነበር፡፡ ስለኾነም ደቡብ አፍሪካውያን በየጊዜው የመብት ጥያቄ ያቀርባሉ፤ ሰሚ ባያገኙም፤ ሀገሬው ሜይ ዴይን ሰበብ አድረጎ የሚያቀርበው ጥያቄ እና የሥራ ማቆም አድማ ግን የዓለም የሥራ ድርጅቶችን ትኩረት ይስባል፤ ምላሽም ይሰጥበታል፡፡

የመብት ጥቄን ተከትሎ የሚደረጉ የሥራ ማቆም አድማዎች የሀገሪቱ ገጽታ ከማጠየሙ ባለፈ ምጣኔ ሃብቱን ማሽመድመዱን ተከትሎ መንግሥት የሠራተኞችን ጥያቄ እንዲያደምጥ እንዳደረገው የታሪክ መምህሩ አስታውሰዋል፡፡ የሰራተኛው መብት፣ ጥቅም፣ የሥራ ቦታ ደህንነት እና ጤንነት በሀገሪቱ ሕግ ኾኖ እንዲወጣም ተድርጓል ነው ያሉት፡፡ በግል ክፍለ ኢኮኖሚው ላይ የሚሰሩ ሠራተኞችም በዓለም አቀፍ የሥራ ስምምነቶች መሠረት መብታቸው እንዲከበር ጅማሬው አለ ብለዋል፡፡

ይኽን ሁሉ ዑደት በየዘመናቱ ያስተናገደው የሠራተኞች ቀን ዘንድሮም በዓለም ለ135ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleትውልዱ ሀገርን በሚያሳድጉ ሜጋ ፕሮጀክቶች እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ።
Next articleየላብ አደሮች ተጋድሎ!