
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ49ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ135ኛ ጊዜ የሚከበረውን የሠራተኞች ቀን “ለሰላም እና ለኑሮ ውድነት መፍትሄ እንሻለን” በሚል መሪ ቃል እያከበረ ይገኛል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፤ በኑሮ ውድነት ምክንያት ሠራተኞች ፈተና ውስጥ መውደቃቸውን ተከትሎ መንግሥት በኑሮ ውድነቱ ላይ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል::ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዝቅተኛ ደሞዝ ወለልን በመወሰንም በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሠራተኞች ቢያንስ መሰረታዊ ነገሮችን ማሟላት እንዲችሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል::
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ በርካታ ሠራተኞች አካላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች እንደደረሰባቸው ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ለዚህም አፋጣኝ የሰላም መፍትሄ ማምጣት ይገባል ብለዋል:: የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው፤ የሠራተኛውን መብት እና ጥቅም ለማስጠበቅ የጋራ ሥራን ይጠይቃል ብለዋል:: የዜጎችን ምርታማነት መጨመር የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የሠራተኞችን የሥራ ላይ ደኅንነት እና ጤንነትን ለመቆጣጠር እና ለመከታተል በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል:: ይህ ደግሞ ምርታማነትን በመጨመር የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም አንድ የመፍትሄ ሀሳብ ነው ብለዋል::
መንግሥት የሠራተኞችን ጥያቄ ለመመለስ ብሎም ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል የኢትዮጵያ ሠራተኞችን ምን ያህል ይጠቅማል የሚለውን ለማየት በጥናት ላይ እንደሚገኝ እና በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል::
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!