
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አብርሃም ኃይሉ እንደገለጹት ባለፉት 9 ወራት ግድቡን ለማጠናቀቅ የሚደረገው ሕዝባዊ ድጋፍ በተለያየ መልኩ ቀጥሏል፡፡
በዘንድሮው በጀት ዓመት በ9 ወራት 1 ቢሊዮን 114 ሚሊዮን 883 ሺህ ብር በላይ ለግድቡ ተሰብስቧል ያሉት አቶ አብርሃም ገቢውም ከሀገር ውስጥ ቦንድ እና ስጦታ፣ ከዲያስፖራ ቦንድ እና ስጦታ እንዲሁም በ8100 አጭር የሞባይል የጽሑፍ መልዕክት አገልግሎት መኾኑን አመላክተዋል።
የግድብ ግንባታ የተጀመረበት 13ኛ ዓመት በመጋቢት ወር መከበሩን አስመልክቶ የተለያዩ የንቅናቄ መድረኮች መካሄዳቸውን የገለጹት አቶ አብርሃም በወቅቱ 182 ሚሊዮን 899 ሺ 52 ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል። በወሩ የተሰበሰበው ገቢም ከ2015 ዓ.ም ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ87 በመቶ እንደሚበልጥ ተገልጿል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 2016 ዓ.ም ከሀገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭ እና ስጦታ፣ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ቦንድ ሽያጭ እና ስጦታ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ገቢዎች ከ19 ቢሊዮን 345 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። በግድቡ ድጋፍ አሰባሰብ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያቅሙን እያበረከተ መኾኑን የገለጹት አቶ አብርሃም ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!