የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማደረግ የሸቀጦች የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት እየሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።

19

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኅላፊ አቶ ሽፈራው አየለ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ እና የምርት አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት እየተሠራ ስለመኾኑ ተናግረዋል። በተለይ በሸማች የሕብረት ሥራ ማኅበራት በኩል መሰረታዊ ምርቶችን ለሸማቾች እየቀረበ እንደኾነ ገልጸዋል። መምሪያው የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ለሸማች ሕብረት ሥራ ማኅበራት ከ20ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም ኅላፊው ገልጸዋል።

አቶ ሽፈራው በዓሉን ምክንያት በማድረግም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ እና ማኅበረሰቡን ለማጨበርበር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ቁጥጥር በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድም መምሪያው ኮሚቴ አዋቅሮ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሸማቾች በግብይት ወቅት ሊፈጸም ከሚችል ማጭበርበር ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም የምሥራቅ ጎጃም ዞን ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኅላፊ አቶ ሽፈራው አየለ ተናግረዋል፡፡ መምሪያው ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር በቅንጂት በመሥራት የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በግብይት ሥርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን ሕገወጥነት ለመከላከል አንጻራዊ ሰላም በሚስተዋልባቸው ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ሥርዓትን ለማስጠበቅ እየተሠራ እንደኾነም አቶ ሽፈራው አየለ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ግብረ ወርቅ ጌታቸው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለ2016/17 የምርት ዘመን እስካሁን ከ12 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ከውጭ ተጓጉዟል።
Next articleየኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የትውልድ ቅብብሎሽ የሚጠይቅ መኾኑን ሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።