የዓለም የላብ አደሮች ቀን

58

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም የላብ አደሮች ቀን የሚከበረው በበርካታ የዓለም ሀገራት የነበሩ ላብ አደሮች ለነጻነታቸው ሲሉ ያደረጉትን ታሪካዊ ትግል እና ያስመዘገቧቸውን ሥኬቶች ለማስታወስ ነው። በካናዳ እና በአሜሪካ የላብ አደሮች ቀን በሚል የሚከበር በዓል ነበር። ዕለቱ ታሰቦ የሚውለው መስከረም በገባ በመጀመሪያው ቀን ነበር። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1889 ዓለም አቀፉ የሶሻሊስት ቡድን እና የንግድ ኅብረት ሥራ የላብ አደሮችን ትግል ለመደገፍ ሚያዚያ 23 ቀንን ለላብ አደሮች መታሠቢያነት እንዲውል እውቅና ሰጥቷል።

ይኽን እውቅና ሲሰጥ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ1886 በቺካጎ ሄይማርኬት አደባባይ የተካሄደውን ሕዝባዊ አመጽ በማሰብ ነበር። ከአምስት ዓመት በኋላ በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ግሩቨር ክሌቭላንድ በሀገሪቱ ቀድሞ በመስከረም ወር የመጀመሪያ ቀን ይከበር የነበረውን ዕለት ግንቦት አንድ ቀን ኾኖ እንዲከበር በሕግ አጽድቋል። ብዙም ሳይቆይ ካናዳም በተሳሳይ ቀን ማክበር ጀመረች።

ከላብ አደሮች ቀን ጋር በተያያዘ በአውሮፓ የምናገኘው ታሪክ ደግሞ መጀመሪያ ሃይማኖት አልባ በኾኑ ሰዎች የሚከበር ፌስቲቫል ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ይኽ አረዳድ ቀስ በቀስ በማኅበራት እና በላብ አደሮች እንቅስቃሴ እየተስተካከለ መስመር ያዘ። በአውሮፓ እና በአሜሪካ ያሉ ላብ አደሮች የካፒታሊዝም ሥርዓትን እንዲጠሉ ያግዛል በሚል እሳቤ የሶቬት ዩኒየን መሪዎችም ይኽን ቀን ደግፈውት ነበር። በሶቬት ቀኑ በትልቁ እየተከበረ የቀጠለ ሲኾን በሞስኮ አደባባዮች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀር በተገኙበት በተለያየ ትዕይንት ይከበር ነበር።

ጀርመን ውስጥ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ1933 ዘግይቶ በይፋ እንዲከበር ታወጀ። ይኽ የኾነው ደግሞ የናዚ ፓርቲ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ነበር። ጀርመን ቀኑን ለይስሙላ እንዲከበር ቢያውጅም ነጻ የኾኑ የላብ አደሮች ማኅበራትን ጎን ለጎን እንዲፈርሱ ታደርግ ነበር። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ከሶቬት መፈራረስ እና በምሥራቅ አውሮፓ የኮምኒስት መንግሥታት መውደቅ ሲጀምሩ በሰፊው ይከበር የነበረው ይኽ ቀን እየፈዘዝ እና እየደበዘዘ መምጣት ጀመረ።

በብዙ የዓለማችን ሀገራት እንደ ሕዝባዊ በዓል የሚቆጠር እና ሰዎች የተለያዩ ጉዞዎችን እና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የሚከበር በዓል ነበር። በዓላማ ደረጃ በላብ አደሮች ላይ የሚደርሰውን የሥራ ጫና ለመቀነስ ይደረግ የነበረን ትግል በማሰብ የሚከበር በዓል ነው:: ወቅቱ የኢንዱስትሪ አብዮት የተቀጣጠለበት ስለነበር በላብ አደሮች ላይ ይፈፀም የነበረውን በደል ለማስወገድ ይደረግ የነበረን የላብ አደሮች ንቅናቄ ለመዘከርም ነው በዓሉ የሚከበረው።

እንደ ዓለም አቀፉ የላብ አደሮች ተቋም መረጃ አሁን ላይ በዓለማችን 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ላብ አደሮች ይገኛሉ። ይህ ቀን በሀገራችንም ለ49ኛ ጊዜ “ለሰላም እና ለኑሮ ውድነት መፍትሄ እንሻለን” በሚል መሪ መልዕክት በመከበር ላይ ይገኛል። ብሪታኒካ እና ዓለም አቀፉ የላብ አደሮች ድረ ገጽ የመረጃ ምንጮቻችን ናቸው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ገበያን የማረገጋት ሚናቸው የጎላ መኾኑ ተገለጸ፡፡
Next articleለ2016/17 የምርት ዘመን እስካሁን ከ12 ሚሊየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ከውጭ ተጓጉዟል።