
ደብረ ብርሃን: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ ገበያን የማረገጋት ሚናቸው የጎላ መኾኑ ተገልጿል፡፡ በከተማ አሥተዳደሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የንግድ ትርኢትና አውደ ርዕይ ተከፍቷል፡፡
በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከመጪው የትንሣኤ በዓል ጋር ተያይዞ ሰፊ ምርት አቅርበዋል፡፡
በንግድ ትርኢትና አውደ ርዕዩ 48 ኢንተርፕራይዞች እና ከ200 በላይ አንቀሳቃሾች ተሳትፈዋል፡፡ የእንሰሳት ተዋጽኦ የእንጨትና ብረታ ብረት ውጤቶች፣ የባልትና ውጤቶች፣ የአልባሳትና ቆዳ ውጤቶች፣ ለጽዳት መጠበቂያ አገልግሎት የሚውሉ ፈሳሽ ሳሙናዎች እና ሌሎችም ምርቶች በንግድ ትርኢትና አውደ ርዕዩ ላይ ቀርበዋል።
አውደ ርዕዩ መዘጋጀቱ ከመጪው የትንሣኤ በዓል ጋር ተያይዞ ገበያን በማረጋጋት ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የምርት አቅራቢዎችና ሸማቾች ተናግረዋል፡፡ አሚኮ በስፍራው ተንቀሳቅሶ እንደተመለከተው የአንድ ዶሮ ዋጋ ከ700 እስከ 800 ብር፣ እንቁላል ዘጠኝ ብር፣ ቂቤ በኪሎ ከ650 እስከ 700 ብር፣ አይብ በኪሎ ከ100 እስከ 150 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው የሚገኘው፡፡
ሸማቾች እንዳሉት በንግድ ትርኢትና አውደ ርዕዩ ያለው የገበያ ኹኔታ የተሻለ ቅናሽ የታየበት ነው፡፡ ይህም ምክንያታዊ ያልኾነ የዋጋ ጭማሬን በመከላከል ቀላል የማይባ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ሥራና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊ ብዟየሁ ሰይድ እንዳሉት የአውደ ርዕዩ መዘጋጀት ዋና ዓላማ በኢንተርፕራይዞችና በሸማቾች መካከል ዘላቂ ግብይትን ታሳቢ ያደረገ ትውውቅ መፍጠር፣ የበዓል ግብይቱ የተሳለጠ እንዲኾን ማድረግ እና በበዓል ወቅት ሊኖር የሚችለውን ያልተገባ የዋጋ ጭማሬ ማስቀረት ነው፡፡
በቀጣይ ቀናት በንግድ ትርኢትና አውደ ርዕዩ የተሻለ እንቅስቃሴ እንደሚኖር ያነሱት መምሪያ ኀላፊው በቦታው ተቀራራቢ በኾኑ የምርት አቅርቦቶች ላይ የጎላ የዋጋ ልዩነት እንዳይኖር ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግም ገልጸዋል፡፡ የንግድ ትርኢትና አውደ ርዕዩ ከሚያዚያ 22 እስከ ሚያዚያ 26/2016 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ ይሆናል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!