ዘመናዊ ማሽን እና የሩዝ ምርት ጥራት

58

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አማራ ክልል የተለያዩ የሰብል ዓይቶች የሚመረትበት ክልል ነው፡፡ በክልሉ ለምግብነት፣ ለውጭ ምንዛሬ እና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል ሰፊ ምርት ይመረታል፡፡ በስፋት ከሚመረቱ ምርቶች መካከል ሩዝ አንደኛው ነው፡፡ ሩዝ በደቡብ ጎንደር ዞን ጣናን ተንተርሰው በሚገኙ ወረዳዎች በስፋት ይመረታል፡፡

ሩዝ ለአርሶ አደሮች ምርት እና ምርታማነትን በመጨመር የአርሶ አደሮችን ሕይዎት የቀየረ ሰብል ነው፡፡ ሩዝ ራስን በምግብ ከመቻል አልፎ ለገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ እያሻሻለ ነው፡፡ መታደል ማሩ በፎገራ ወረዳ የወጅ ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው፡፡ ሩዝ ከመጣ ጀምሮ ገበሬው ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ይላሉ፡፡

ምርቱን አሳድጎታል፤ ሩዝ ግብዓት ከተሟላለት ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ የሰብል ዓይነት ነው ብለዋል፡፡ ሩዝ ለምግብ ፍጆታ ከመዋል ባለፈ ለገበያ እንደሚያቀርቡም ተናግረዋል፡፡ በእርሳቸው አጠራር “ሁለት ቀዳማ መሬት” ያለው አርሶ አደር አንደኛውን ለቀለብ ቢያስቀምጥ የአንደኛው ምርት ግን ለገበያ ያቀርባል ነው ያሉት፡፡

የሩዝ ገበያ ጥሩ ነው የሚሉት አርሶ አደር መታደል አርሶ አደሮች ለገበያ የሚያቀርቡ አንድ ጊዜ ስለኾነ ይጎዳሉ ብለዋል፡፡ ገበያው የተመቻቸ እና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ ቢኾን የበለጠ ተጠቃሚ ያደርጋል ይላሉ፡፡ የፎገራ ሩዝ ከውጩ ሩዝ ጋር ሲነጻጸር ዋጋው አነስተኛ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህን ለውጥ ያመጣውም የመፈልፈያ ማሽኑ እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡

የውጭ ሩዝ በዘመናዊ ማሽን ስለሚፈለፈል ሩዙ ሳይጎዳ ስለሚያወጣው ገበያ ላይ የተሻለ ተቀባይነትን ያገኛል። የሀገር ውስጡ ግን መፈልፈያ ማሽኑ ስለ ሚከካው እና በጥራት ስለማይፈለፍለው ዋጋው ይቀንሳል ነው ያሉት፡፡ ማሽኑ ዘመናዊ ከኾነ ግን የፎገራ ሩዝ ዋጋውም ከውጩ ሩዝ ጋር መስተካከል እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡

ዘመናዊ ማሽን እንዲመጣላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ይመጣሉ እየተባሉ ሳይመጣላቸው መቅረቱን ገልጸዋል፡፡ ዘመናዊ ማሽኖችን መጠቀም ከቻልን ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይኾን ለውጭ ገበያም የማቅረብ አቅም አለን ነው ያሉት፡፡ ምርትን ወደ ውጭ ለመላክ እንድንችል ግን ዘመናዊ ማሽን ያስፈልገናል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት ፎገራ ብሔራዊ የሩዝ ምርምር እና ሥልጠና ማዕከል ዳይሬክተር እና ተመራማሪ ፍስሃ ወረደ (ዶ.ር) ለዓመታት የቀጠለ ለምርምር የሚኾኑ የሩዝ ዓይነቶችን ከውጭ በማስመጣት ሲፈትሹ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለአካባቢው ተስማሚ መኾናቸው፣ የተሻለ ምርት መስጠታቸው፣ በሽታ መከላከላቸው እና ድርቅን መቋቋማቸውን እያዩ የዝርያ መምረጥ ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡ ከ30 በላይ ዝርያዎች ለአርሶ አደሮች እንዲደርሱ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

የሰብል አያያዝ እና እንክብካቤ ላይም ምርምር እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት፡፡ በሽታ እና ተባይ የሚቋቋሙ ዝርያዎችን የመምረጥ፣ ለበሽታ ፍቱን መድኃኒቶችን የመምረጥ ሥራ ሲሠሩ መቆየታቸውን አንስተዋል፡፡ ሜካይናዜሽን ላይም እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት፡፡ ሩዝ ከሌሎች ሰብሎች በተለየ መልኩ መፈልፈል እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ ምርምሩን የማያሳየት እና የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሠራ አመላክተዋል፡፡ ምርታማነትን የሚጨምሩ ዝርያዎችን እንደሚሰጡም ገልጸዋል፡፡ ያልተቀላቀሉ እና ያልቆዩ ዝርያዎችን በመጠቀም እና በተገቢው መንገድ በማምረት የተሻለ ምርት ማምረት እንደሚቻልም አንስተዋል፡፡ የሩዝ መፈልፈያ ማሽኖች በምርት ጥራት ላይ ለውጥ እንደሚያመጡ የተናገሩት ዳይሬክተሩ አብዛኛዎቹ ማሽኖች የቆዩ በመኾናቸው ሩዙን ይሰባብራሉ ነው ያሉት፡፡ ዘመናዊ ማሽኖች መሰባበርን እንደሚቀንሱም ተናግረዋል፡፡ እንደ ዝርያው ቅርጽ፣ ውፍረት፣ ቀለም፣ ርዝመት ማሽኖች በሚፈለፍሉበት ወቅትም ማስተካከል ይገባልም ብለዋል፡፡ የእርጥበት መጠንም ጥራት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ነው የተናገሩት፡፡ የጥራት መጠኑ መቀነስንም በገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንደማያደርግ ነው የገለጹት፡፡

ከውጭ ተፈልፍለው የሚመጡ ሩዞች ቀጠን እና ረዘም ያሉ ናቸው የሚሉት ዳይሬክተሩ እንዲህ ዓይነት ሩዞች የሚገኙት ቅዝቃዜ በሌለበት አካባቢ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ እነዚህ የሩዝ ዓይነቶች በኢትዮጵያ መብቀል የሚችሉት በሞቃታማ አካባቢዎች ነው ብለዋል፡፡ ከውጭ የሚመጣውን ዓይነት ምርት ከተፈለገ ቀጫጭን እና ረጃጅም ዝርያዎችን ቅዝቃዜ በሌለባቸው አካባቢዎች በመዝራት በዘመናዊ ማሽኖች መፈልፈል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የማሽኖቹ ዋጋ ከፍ ያለ በመኾኑ ለአርሶ አደሮች ማሽኖችን ማቅረብ እንደሚቸገሩም አንስተዋል፡፡ መንግሥት ማሽኖችን ማቅረብ የሚችል ከኾነ የምርት ጥራትን በማሳደግ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል ነው ያሉት፡፡ ግብርና ቢሮ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚኾኑበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት ብለዋል፡፡

ሩዝ ላይ የነበረው ትኩረት አናሳ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረት እያገኘ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ለስንዴ ምርታማነት የተደረገው እንቅስቃሴ ለሩዝም መደረግ አለበት ነው ያሉት፡፡ ሩዝ የሚመረትባቸውን አካባቢዎች መለየት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) የሩዝ ሰብል ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ክትትል እየተደረገበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ሩዝ በፊት ውኃማ አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ ይለማ የነበረ ሰብል እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ግን በርካታ የሩዝ ዝርያዎች በምርምር በመገኘታቸው ውኃማ ባልኾኑ አካባቢዎች ማልማት እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

ለሩዝ ምርት የግብዓት አቅርቦት እና የኩታገጠም አስተራረስ ዘዴም ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል፡፡ ሩዝ በክልሉ መንግሥት ብቻ ሳይኾን በፌዴራል መንግሥት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ነው የተናገሩት፡፡ የአማራ ክልል በሩዝ ምርት ቀዳሚው መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

ዘመኑን የዋጁ የመፈልፈያ ማሽኖች አለመኖራቸው የሩዝን ጥራት እና መጠን እንደሚቀንሱም ገልጸዋል፡፡ የሩዝ መፈልፈያ ማሽኖችን ዘመናዊ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራበት መኾኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በማሽኖች ዙሪያ የሚነሳውን ጥያቄ እንደሚቀርፍም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡ የሩዝ ምርትን እሴትን ጨምሮ ለገበያ ማቅረብም ትኩረት ይደረግበታል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleማኅበረሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመኾን ለአካባቢው ሰላም እየሠራ መኾኑ ተጠቆመ።
Next articleጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ገበያን የማረገጋት ሚናቸው የጎላ መኾኑ ተገለጸ፡፡