
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በመሀል ሜዳ ከተማ ከባለሃብቶች ጋር በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳይ እና በልማት ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የኮማንዶ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ሳዲቅ አህመድ ጽንፈኛ ኃይሎች ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በኾነ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ለመፈጸም ቢሞክሩም የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመኾን እኩይ ድርጊታቸውን አክሽፏል ነው ያሉት።
የሀገርን ሰላም ስጋት ላይ የሚጥል ተግባር ከመፈጸም ይልቅ ለሀገራዊ ሥልጣኔ እና ዕድገት በመትጋት የአባቶቻችንን ታሪክ በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። የመሀል ሜዳ ከተማ ከንቲባ መሳይ ንጉሴ በበኩላቸው ጽንፈኛው ከደገሰልን የውርደት ሴራ ራሳችንን ጠብቀን ሀገርን በመስዋዕትነት እያጸና ከሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ጎን ተሰልፈን የተገኘውን ሰላም ማጽናት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ተወያይ ባለሃብቶቹ በመድረኩ ላይ በሰጡት አስተያየት የሀገራችን ዕድገት በሰላም እጦት ሊስተጓጎል አይገባም ብለዋል፡፡ የሀገራችንን ሚስጢር ለታሪካዊ ጠላቶቻችን አሳልፎ መስጠት አይገባም ፤ ጽንፈኛውም እየሠራ ያለው ይህንኑ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ለሀገራችን እድገት ዋስትናው ጽንፈኝነት ሳይኾን ለሰላም ዘብ መቆም እና ለልማት እጃችንን መዘርጋት መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ ተፈቃቅሮ እና ተከባብሮ መኖር ያስፈልጋል ያሉት ባላሃብቶቹ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ለመናድ የተነሳውን ጎጠኛ ኃይል እንደማይደግፉ ተናግረዋል፡፡
በመኾኑም ለሰላማችን ከፀጥታ ኃይሎች እና ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ነን ብለዋል፡፡
መረጃው፡- የመከላከያ ሠራዊት ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!