
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ምስጋናው ንጋቱ ይባላሉ፡፡ ነዋሪነታቸው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምሥራቅ በለሳ ወረዳ አርባጸጓር ቀበሌ ነው፡፡ በተከታታይ ዓመታት የተፈጠረው የዝናብ እጥረት ሕይወታቸውን እንዳከበደባቸው ይናገራሉ፡፡ በ2015/16 የምርት ዘመን አራት ጊዜ ብቻ ነው ዝናብ የዘነበው፤ ይሄውም ዝቅተኛ እና መካከለኛ የሚባል አይነት ዝናብ ነው፤ ዘርተን ያመረትነው ምርት የለም፤ ለእንስሳት የሚኾን መኖም አልበቀለም ነው ያሉት፡፡
ቀደም ሲል በአሥር ዓመታት እና በሰባት ዓመታት ልዩነት ድርቅ ይከሰት እንደነበር ያስታወሱት ባለታሪካችን ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ድርቅ ተከስቷል ብለዋል። ድርቁ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ነው የመጣው ብለዋል፡፡ አስቸኳይ ድጋፍ ካልተደረገልን ከመራብ አልፈን እንሞታለን ነው ያሉት፡፡ ዘንድሮ የገጠመን ድርቅ ከባድ እና አስከፊ ነውም ብለዋል፡፡ “ዘርተን ያመረትነው ምርት የለም፤ ለእንስሳት የሚኾን መኖም አልበቀለም፣ እርዳታ እንሻለን” ሲሉ ነው የተናገሩት።
በሬዎቻችን ደክመዋል፤ ያስቀመጥነው ዘርም የለም፤ በቀጣይ ለማረስ እንቸገራለን፣ በአካባቢው እርዳታ ባለመኖሩ አቅማቸው የፈቀደ ሰዎች እርዳታ ወደሚደረግባቸው ሌሎች ዞኖች እየሄዱ ነው ይላሉ፡፡ መንግሥት ችግራችን በአፋጣኝ መፍታት አለበት፤ ሰሚ እንዲኖረን እንፈልጋለን፣ አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠን ረሃብ ይገድለናል ብለዋል፡፡ የእንስሳት መኖ ድጋፍ ካልተደረገ ከብቶቻቸውን እንደሚያጧቸውም ነው የተናገሩት፡፡ ቀይ መስቀል እና የክልሉ ውኃ ቢሮ ላደረጉላቸው ድጋፍ አመሰግነዋል፤ ሌሎች ተቋማትም እንዲደግፏቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማሥተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በድርቁ ምክንያት ከምግብ እጥረት ባለፈ የውኃ እጥረት እና የመኖ አቅርቦት ችግር መኖሩን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮች በችግር ውስጥ ኾነው ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ እንስሳትን እያኖሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከል ዐቢይ ኮሚቴ ችግሩን መገምገሙንም አስታውቀዋል፡፡ ሰሜን ጎንደር እና ዋግ ኽምራ ብሔሰረብ አሥተዳደር ላይ የተሻለ ድጋፍ ቢኖርም ማዕከላዊ ጎንደር ላይ ጉድለት አለ ነው ያሉት፡፡ ማዕከላዊ ጎንደር ላይ በእንስሳት ብቻ ሳይኾን በምግብ አቅርቦት ላይም በወቅቱ እንደማይደርስ ነው የተናገሩት፡፡ በዐቢይ ኮሚቴው ግምገማ መሠረት ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ለድርቅ ሁሉን አቀፍ ሥራ መሠራት እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል፡፡ የመድኃኒት፣ የምግብ፣ የውኃ እና የመኖ አቅርቦት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያሉት፡፡ በቀጣይም የድርቅ ችግር ሊገጥም ይችላል ያሉት ኮሚሽነሩ መጠባበቂያ ለመያዝ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
በተከዜ ተፋሰስ የሚፈጠረውን ድርቅ በዘላቂነት ለመፍታት የተለየ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡ ችግር በተነሳ ቁጥር ምላሽ እየሰጡ መሄድ አዋጭ አለመኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ይልቁንም ቅድመ ጥንቃቄ እና ዝግጁነት ያስፈልጋል ነው ያሉት። አሁን በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ለመታደግ መላው ኢትዮጵያውያን፣ ረጂ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት የችግሩን ስፋት ተገንዝበው ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!