በአማራ ክልል በ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጀት 497 የከተማ ልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መኾኑ ተገለጸ።

20

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የከተሞችን ዘላቂ እድገት ለማሳለጥ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የክልሉ ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታውቋል። በቢሮው የመሰረተ ልማት ተቋማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ አሻግሬ አቤልነህ እንደገለጹት በከተሞች 497 የልማት ፕሮጀክቶች በመከናወን ላይ ናቸው።

የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶቹ ግንባታ ወጪ የክልሉ መንግሥት በመደበው 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እና ቀሪው በከተሞቹ አቅም የሚሸፈን መኾኑን ተናግረዋል። ፕሮጀክቶቹ እየተከናወኑ ያሉት በ29 የክልሉ ከተሞች ሲሆን በደሴ፣ ጎንደር፣ ኮምቦልቻ እና ባሕር ዳር ከተሞች ነው። የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛልም ብለዋል።

እየተገነቡ ከሚገኙ የመሰረተ ልማት ሥራዎች መካከል 18 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣ 56 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የጠጠር እና 9 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገዶች ይገኙበታል። ከእዚህ በተጨማሪ 11 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር መብራት፣ 32 መለስተኛ ድልድዮች፣ 5 ሄክታር የአረንጓዴ ልማት፣ 30 ሼዶች፣ የመናኽሪያ ግንባታዎች እንዲሁም የድጋፍ ግንብ እና ሌሎች የልማት ሥራዎች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።

የልማት ፕሮጀክቶቹ እስከበጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሠራ መኾኑንም አቶ አሻግሬ ጠቁመዋል። ፕሮጀክቶቹ ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎችም የሥራ ዕድል እንደፈጠሩም ለኢዜአ ገልጸዋል። ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ሲበቁ በከተሞቹ ዘላቂ ልማትን ከማረጋገጥ ባለፈ ከተሞቹን ለኑሮ ምቹና ተመራጭ እንዲኾኑ የሚያግዙ መኾናቸውንም አቶ አሻግሬ ተናግረዋል።

በደሴ ከተማ እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶች የከተማዋን ዕድገት በማፋጠን ሁለተናዊ ተጠቃሚነታችንን የሚያረጋግጡ ናቸው ሲሉ የገለጹት የከተማዋ ነዋሪ ቄስ መላኩ ዳኛው ናቸው። በተለይ ዘንድሮ የሕዝብን የረጅም ጊዜ የልማት ጥያቄዎች የመለሱ የአስፋልት መንገድ፣ የመናኽሪያ፣ የድልድይ እና መሰል የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን ገልጸዋል።

“የአካባቢያችንን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ለልማት ሥራው በገንዘብና በጉልበት ድጋፍ እያደረገን ነው” ያሉት ቄስ መላኩ፣ የልማት ሥራዎቹ ፈጥነው እንዲጠናቀቁ የድርሻዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው” ዲያቆን ተስፋው ባታብል
Next articleበተደረገው ሕግ የማስከበር ዘመቻም በርካታ የጦር መሳሪያ እና የጽንፈኛው አባላት መማረካቸውን የአካባቢው ኮማንድፖስት አስታወቀ።