“ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ወገኖች የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው” ዲያቆን ተስፋው ባታብል

51

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በድርቅ እና በሕወሓት ታጣቂዎች ወረራ ምክንያት በርካታ ወገኖች ለችግር መዳረጋቸውን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በድርቅ ከተጎዱ ወገኖች በተጨማሪ ከሌሎች ክልሎች ተፈናቅለው የመጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች በክልሉ ይኖራሉ፡፡ የሕወሓት ታጣቂዎች በሰሜን ወሎ ራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ እና አላማጣ ከተማ፣ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኮረም፣ ወፍላ እና ዛታ ወረዳዎች በፈጠሩት ወረራ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ተፈናቅለው የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊ ኾነዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማሥተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል ባለፉት ዓመታት በክልሉ በርካታ ችግሮች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ለሰዎች ሞት፣ መቁሰል፣ መፈናቀል፣ የሃብት እና ንብረት መውደም እና የሥነ ልቦና ስብራት መፈጠሩን አንስተዋል፡፡
ከሰሜኑ ጦርነት ጉዳቶች ለማገገም ሲሠራ በነበረበት ወቅት በክልሉ የፀጥታ ችግር መፈጠሩን ነው የተናገሩት፡፡ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት የማኅበረሰቡን ኑሮ ከድጡ ወደማጡ የወሰደ እና ለበርካታ ሥራዎች እንቅፋት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር ሰላማዊ እንቅስቃሴውን በመገደቡ ግብዓት እና የሰብዓዊ ድጋፍ በተፈለገው ልክ እየቀረበ አለመኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሠርተው እየበሉ አለመኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ አርሶ አደሮችንም በወቅቱ የግብርና ሥራቸውን እንዳያከናውኑ እያደረጋቸው ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ የተፈጠረው ድርቅ ፈተና እንደኾባቸው ነው የተናገሩት፡፡ የድርቁ ሽፋን ሰፊ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ 9 ዞኖችን እና 43 ወረዳዎችን ያጠቃው ድርቁ 1 ሚሊዮን 846 ሺህ 955 ወገኖችን ጎድቷል ብለዋል፡፡ ድርቁ ያደረሰው ጉዳት ከፀጥታ ችግሩ ጋር ተዳምሮ ውስብስብ እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡

በልዩ ልዩ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በክልሉ መጠለያ ጣቢያ እና ከማኅበሰረቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ወገኖች መኖራቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ለተፈናቃይ ወገኖችም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያት ተፈናቅለው በክልሉ የሚኖሩ ወገኖችም 621 ሺህ 980 በላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ 98 ሺህ 630 የሚኾኑት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡

ሕወሓት በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች መፈናቀላቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በሕወሓት ወረራ ምክንያት የተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማድረግ ሌላ ጫና መፍጠሩንም አንስተዋል፡፡ በሕወሓት ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖችም እርዳታ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል፡፡ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን ነው ያሉት፡፡ በክልሉ በአጠቃላይ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ወገኖች ድጋፍ እየተደረገላቸው መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት የተፈጠሩትን ችግሮች ታሳቢ በማድረግ የአደጋ ምላሽ እየሠጠ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና በባንኮችም ድጋፍ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡ መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶችም 188 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡ ድጋፋቸው ለመድኃኒት እና ለእንስሳት መኖ አቅርቦት ጥቅም ላይ መዋሉንም አንስተዋል፡፡ ረጂ ድርጅቶችም ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥትም የሚያዚያ ወርን ሳይጨምር ለአራት ዙር ድጋፍ ማድረጉን ነው የተናገሩት፡፡ የፀጥታ ችግሩ ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማሰራጨት እንቅፋት እንደኾነባቸው አስታውቀዋል፡፡ በሚያዚያ ወርም ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የገጠመውን ችግር ለመቀልበስ የሚያስችሉ ውይይቶች መደረጋቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ በተቻለ መጠን ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የተጎጂዎችን ቁጥር በአግባቡ አለመለየት ሌላኛው ችግር እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ ተጠቃሚዎችን ብቻ ለይቶ ማስተናገድ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው እርዳታ ወደ ብር ሲቀየር 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በወር ወጪ እንደሚኾ ነው ያነሱት፡፡ መንግሥት ብቻውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚቸገርም አንስተዋል፡፡

ትክክለኛ ተጎጂዎችን የመለየቱን ሥራ በአግባቡ መሥራት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ ድጋፉ እስከ ኅዳር 30/2017 ዓ.ም ድረስ መቀጠል አለበት ያሉት ኮሚሽነሩ የተጎዱ ወገኖች አምርተው ሊጠቀሙ የሚችሉት ከኅዳር 30 በኋላ መኾኑን አመላክተዋል፡፡ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡ ረጂ ድርጅቶችም ድጋፋቸውን አስፍተው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

ማኅበረሰቡ፣ በጎ አድራጊ ድርጅቶች እና ሌሎችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የድጋፍ ትንሽ የለውም ያሉት ኮሚሽነሩ ያለው ለሌለው ማካፈል አለበት፣ በትብብር ከሠራን ችግሩን መሻገር እንችላለን ብለዋል፡፡

ክርስቲያኖች የትንሳኤ በዓልን ሲያከብሩ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት መኾን አለበት ነው ያሉት፡፡ ቸርነት ማድረግ ዋጋው ብዙ ነው ያሉት ዲያቆን ተስፋው ጾሙ ሰብዓዊነትን፣ ልግስናን፣ ቸርነትን፣ ከራስ በላይ ለሰዎች ማሰብን ያስተምራል፤ ይሄን ቸርነት ለተጎዱ ወገኖች ማዋል ይገባል ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን የለውጥ አራማጆችን የማብቃት ሥራ አጠናክራ ትቀጥላለች” የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዚዳንት ዛዲግ አብርሃ
Next articleበአማራ ክልል በ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጀት 497 የከተማ ልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መኾኑ ተገለጸ።