
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ተጠርጥረው ሥልጠና የወሰዱ ዜጎች ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል። ሠልጣኞቹ በተለያዩ የፀጥታ ችግሮች ተጠርጥረው ለ7ኛ ዙር ሥልጠና ሲሰጣቸው የቆዩ ናቸው፡፡
ሥልጠናውን ከወሰዱት መካከል ዋና ሳጅን አሰፋ ባየ በሥልጠናው የሰላምን አስፈላጊነት እና ምንነት ተምረንበታል፤ ሁሉም ነገር የሚገኘው ከሰላም ስለኾነም ስለ ሰላም መሥራት አለብን ብለዋል፡፡ በቆይታችን ብዙ ነገር ተምረናልም ነው ያሉት፡፡ አቶ አሰፋ በሰላም እጦቱ ሀገራችን ምን ያህል ወደ ኋላ እንደቀረች እና የሕጻናት እና የአዛውንቱን መጎዳት ተረድተናል፤ ሁላችንም ለሰላም መዘመር አለብን ነው ያሉት፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ጌታሰው ንብረት በተሃድሶ ሥልጠናው ስለ ሰላም አሥፈላጊነት መሠልጠናቸውን እና ትልቅ ትምህርት እንዳገኙበትም ገልጸዋል፡፡ በየዕለቱ እንቅስቃሴያችን ያማረ የሚኾነው ሰላም ሲኖር ነው ብለዋል፡፡ በሰላም እጦት ሁሉም ተጎጂ ስለሚኾን የሰላምን አስፈላጊነትን ለማኅበረሰቡ እንደሚያስተምሩ ተናግረዋል፡፡
በመከላከያ ሚኒስቴር የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሌተናል ኮሎኔል ዳዊት እንዳለ በፀጥታው ችግር ምክንያት በክልሉ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴው ችግር እንዳጋጠመው እና ሕዝቡም እየተቸገረ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ ክልሉን እና ሕዝቡን ከጥፋት ለመታደግ ሲባል በተወሰደ እርምጃ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ከምክር እና ሥልጠና ሲመለሱም የማኅበረሰቡን ሰላም ለማስጠበቅ እንዲያስተምሩ እና እንዲተባበሩ አሳስበዋል፡፡ በማወቅም ባለማወቅም በግጭቱ ተሳታፊነት የቀጠሉትን ወገኖች መክረው እንዲመልሱም አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
