“ለፍትሕ ሥርዓት መቃናት የዜጎች ተሳትፎ የላቀ ነው” ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

12

ደሴ: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ስትሪንግ ኮሚቴ በኮምቦልቻ ከተማ ከማኅበረሰቡ ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ፍትሕ መምሪያ ኀላፊ መሀመድ አወል መንግሥት ለባለሃብቶች የሚያስረክበው መሬት በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን በማረጋገጥ እና ብልሹ አሠራሮችን ከማስወገድ አኳያ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ የፍትሕ አሰጣጡን ለማዘመን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመሥራት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን አቶ መሀመድ ገልጸዋል። የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም የሀሰተኛ ምስክር እና ሀሰተኛ ማስረጃ መስጠት እየተበራከተ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡ እንዲኹም የዳኝነት ነጻነትን የሚጋፉ ጣልቃ ገብነት መኖር፣ በፍርድ ቤት በተያዘ ጉዳይ ላይ የሚዲያ መግለጫ መስጠት እና አላስፈላጊ ተፅዕኖ መኖር በፍትሕ ዘርፉ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች መኾናቸውን ተናግረዋል።

የፍትሕ ዘርፍ ኢንፎርሜሽን ስትሪንግ ኮሚቴ ሪፎርሙን በመተግበር የፍትሕ ሥርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሠራም አብራርተዋል፡፡ በቀጣይ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት ይሠራል ሲሉ ኀላፊው ጠቁመዋል። የአማራ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ሁሉም የሕግ አካላት የፍትሕ ሥርዓቱን ማዘመን አለበት ብለዋል።

ለፍትሕ ሥርዓት መቃናት የዜጎች ተሳትፎ የላቀ ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ የሚታዩ ችግሮችን ለማስተካከል እና ፍትሕን ለማረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ዳኞች፣ የፍትሕ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈውበታል።

ዘጋቢ፡- ሰልሀዲን ሰይድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለመኸር ሰብል ልማት መሳካት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳዳር አሳሰበ፡፡
Next article“ሠልጣኞች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በግጭቱ ተሳታፊነት የቀጠሉ ወገኖችን መክረው ሊመልሱ ይገባል” ሌተናል ኮሎኔል ዳዊት እንዳለ