ለመኸር ሰብል ልማት መሳካት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳዳር አሳሰበ፡፡

18

እንጅባራ: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)መምሪው የ2016/17 የመኸር ሰብል ልማት ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ ያተኮረ እና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ውይይት በእንጅባራ ከተማ አካሂዷል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና ዘላቂ ሰላምን ማጽናት እኩል ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኾናቸውን ገልጸዋል።

በአብዛኛዎቹ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትርፍ አምራች አካባቢዎች በግጭት ምክንያት ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን አንስተዋል፡፡ ዋና አሥተዳዳሪው ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው በመመለስ የክረምት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ከሰላም ማስከበር ሥራ ጎን ለጎን ለመኸር ሰብል ልማት መሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባም ዋና አሥተዳዳሪው አሳስበዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ አስፋው (ዶ.ር) በበጋ ወራት በተለያዩ ምክንያቶች ያጋጠመውን የምርት መቀነስ በመኸር ሰብል ልማት ለማካካስ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። የማሣ ልየታ፣ የእርሻ ድግግሞሽ፣ የዘር እና የማዳበሪያ አቅርቦት በወቅቱ መከናወናቸው ከተደረጉ የቅድመ ዝግጅቶች ሥራዎች መካካል እንደኾኑም መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል።

በምርት ዘመኑ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ338 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የመኸር ሰብሎች ይሸፈናል፡፡ ከዚህ ውስጥም ከ187 ሺህ ሄክታር በላይ የሚኾነው መሬት በኩታገጠም የሚታረስ መኾኑን ኀላፊው አንስተዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ለመኸር ሰብል ልማት ከሚያስፈልገው 842 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ 56 በመቶ የሚኾነው ወደ ብሔረሰብ አሥተዳደሩ ገብቶ ለአርሶ አደሮች እየተሰራጨ እንደኾነም ገልጸዋል።

በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በምርት ዘመኑ በመኸር ሰብል ከሚለማው ማሳ ከ14 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መሰረተ ልማትን በማሻሻል የሕዝባችንን ጤና መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሥራ ዕድሎችንም እየፈጠርን ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“ለፍትሕ ሥርዓት መቃናት የዜጎች ተሳትፎ የላቀ ነው” ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ