
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአንድ ወር በፊት የኮሪደር ልማት ስራ ሂደት ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አጠቃላይ ግምገማ አድርገን ነበር ብለዋል። ዛሬ እንደገና ከአዲስ አበባ አሥተዳደር አመራሮች እና የኮሪደር ልማት ሥራ መሪዎች ጋር በመገናኘት በሥራዎቻችን ርምጃ ዙሪያ ጥልቀት ያለው ውይይት አድርገናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
እነኚህ ሥራዎቻችን የግንባታ ብቻ ጉዳዮች አይደሉም፤ ይልቁንም ከተማችንን ወደ ላቀ ምቹ፣ ንቁ እና ዘላቂ የመኖሪያ ከባቢ የመለወጥ ጥረቶች ናቸው ነው ያሉት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)ሥነ ውበትን በማሳደግ፣ አረንጓዴነትን በማስፋት ብሎም መሰረተ ልማትን በማሻሻል የሕዝባችንን ጤና መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሥራ ዕድሎችንም እየፈጠርን ነው ብለዋል።
በጋራ እነዚህ ጥረቶቻችን የአዲስአበባን አጠቃላይ ይዞታ በማላቅ እውነትም ለሁሉም ነዋሪዎቿ ፍላጎቶች የተመቸች እንደሚያደርጋት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ መልእክት አጋርተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!