
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተቋሙ በትጋት እንዲሠራ ቋሚ ኮሚቴዉ አሳስቧል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቁን ጠቅሶ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ተቋሙ በትጋት እንዲሠራ የውኃ፣ መስኖ እና ቆላማ አካባቢ እንዲሁም አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል፡፡ ከጥናት እና ዲዛይን ሥራ አንጻርም ፕሮጀክቶችን በዕቅዱ መሰረት ከማከናወን አንጻር ዝቅተኛ አፈጻጸም መኖሩን አንስቷል፡፡
እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ ተቋሙ በትኩረት እንዲሠራ ኅብረተሰቡ መጠየቁንም ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ዲዛይን ሂደት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ለፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያቱ የዲዛይን ሠነድ ችግር መኾኑን ጠቅሰው ወደ ግንባታ ለመግባት በጀት እየተጠባበቁ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመኾን ሀገራዊ የዲዛይን ሠነድ ኮድ እንዲዘጋጅ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
ኤፍቢሲ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ያላትን አጠቃላይ የመስኖ አቅም መረጃ እና ቀጣይ የፖሊሲ አቅጣጫ ጥናት በማድረግ 10 ሚሊዮን ሄክታር በመስኖ መልማት የሚችል መሬት እንዳላት ማወቅ ተችሏል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!