
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በ2016 በጀት ዓመት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ከ11 በላይ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ ይገኛሉ። በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ተሻገር አዳሙ በከተማ አሥተዳደሩ በፌዴራል መንግሥት ትላልቅ ፕሮጀክች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪ በከተማ አሥተዳዳሩ እና በዓለም ባንክ በጀት በ962 ሚሊዮን ብር በጀት 22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፋል መንገድ እየተሠራ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ 50 በመቶው በተያዘው በጀት ዓመት ይጠናቀቃል። በአጼ ቴዎድሮስ፣ በግሺ ዓባይ እና በላይ ዘለቀ ክፍለ ከተሞችም 2 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር፣ በዘጌ ሳተላይት ከተማ የ11 ኪሎ ሜትር መንገድ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
ከአምስት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን በሶላር የሚሠራ የመንገድ ዳር መብራቶችን እና በቀለም የመንገድ ላይ ምልክቶችን እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በዛሬው እለትም በከተማ አሥተዳደሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል። ከዚህ ውስጥ በ1 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈው የዲፖ ሁለተኛ ዙር አረንጓዴ ልማት እና መናፈሻ ሥራ አንዱ ነው። ፕሮጀክቱ በ335 ቀናት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። 94 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል። ሥራው ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ለከተማዋ ነዋሪዎች ተጨማሪ መዝናኛ ከመኾኑም ባሻገር የከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ በማስፋት ሚናው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በጣና እና ዳግማዊ ምኒልክ ክፍለ ከተሞች 2 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ የማስጀመር ሥራ ተከናውኗል። በከተማው የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማኅበረሰቡ ለማስተዋወቅ የሚያገለግሉ በ24 ሚሊዮን ብር ወጭ የሚሠራ የዲጅታል ቢል ቦርድ ተከላ ሥራም ይገኝበታል።
የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እና ጥራት እንዲጠናቀቁ ተቋራጮች እና ማኅበረሰቡ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባለፉት ወራት የተከሰተው የፀጥታ ችግር ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ ማድረጉን አንስተዋል፡፡ አሁን ላይ በተገኘው ሰላም ከተማዋን ለጎብኝዎች ምቹ፣ በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ተመራጭ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በምክትል ርዕስ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) በጣና ዙሪያ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ከተማዋን ከማስዋብ ባለፈ የጣናን ደኅንነት በመጠበቅ የጎላ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል። ግብርና ቢሮም በሚሠሩ ሥራዎች አጋዥ መኾኑን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!