
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ የሥራ ቆይታ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዡዩአንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አሰናብታዋል። አምባሳደር ታዬ፤ ዣኦ ዡዩአን በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያደረጉትን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
በተለይም በሁለቱ ሀገራት ያለው ትብብር በወቅቶች የማይቀያየር ስትራቴጂያዊ አጋርነት ደረጃ ላይ መድረሱ ሀገራቱ የገነቡት ግንኙነት ልዩ፣ ጠንካራ እና አርዓያነት ያለው መሆኑን እንደሚያረጋጥ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል ቻይና ያደረገችው ድጋፍ የሁለቱ ሀገራት የረዥም ዘመን ጠንካራ ወዳጅነት ሌላኛው ማሳያ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህም የአምባሳደሩን በኢትዮጵያ የነበራቸውን የሥራ ቆይታ ልዩ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአምባሳደሩ የሥራ ቆይታ ወቅት በቻይና መንግሥት ድጋፍ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በኢትዮጵያ መጠናቀቃቸውን አምባሳደር ታዬ አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መኾኗን ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!