
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ዜጎቿ መካከል 84 በመቶው የሚኾነው በግብርና ሥራ እንደሚተዳዳሩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴያቸው በግብርና ላይ ጥገኛ የኾኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ለግብርና ዘርፍ ትኩረት መሥጠት የምርጫ ጉዳይ ሳይኾን ግዴታም ጭምር ነው።
ይህንን የሀገር መሠረት የኾነ ምጣኔ ሃብታዊ ምሰሶ ለማዘመን እና ምርታማነትን ለማሳደግ ደግሞ ዘርፉን ከኋላቀር የግብርና አሠራር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ ያስፈልጋል። የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ሽግግር እና እድገትን እንዲቆናጠጥ ትኩረት መስጠት ይገባል።
ለመኾኑ ክልሉ ግብርናውን ለማዘመን እና ምርታማነትን ለማሳደግ ምን እየተሠራ ይኾን?
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት በክልሉ በ2016/17 የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ትኩረት ተደርጓል። 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርትም ለማግኘት ታቅዷል።
ከባለፈው የምርት ዘመን ከተገኘው ምርት በ24 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ብልጫ ለማስመዝገብ እየተሠራ ይገኛል። ምርታማነቱን ደግሞ በአማካይ በሄክታር ወደ 32 ኩንታል ለማድረስ እየተሠራ ይገኛል። በምርት ዘመኑ የምግብ ፍላጎትን ማሳካት፣ በክልሉ እየተስፋፉ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሚውል በቂ ግብዓት ማሟላት እና ወደ ውጭ የሚላኩ (ኤክስፖርት) ምርቶች ላይ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጅዎችን እና ግብዓቶችን በሙሉ ፓኬጅ ለመጠቀም እንዲኹም ለምርታማነት እድገት ማነቆ በኾኑ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተደርጓል። ለምርት መቀነስ ምክንያት የኾኑ በሰብል ላይ የሚከሰቱ ተባዮችን እና በሽታዎችን መከላከል ላይም ትኩረት ተደርጓል። የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል ከ650 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ ጥቅም ላይ ለማዋል መታቀዱን ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ የጥቁር አፈር ፓኬጅን ተግባራዊ ማድረግ እና የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀምን ማሻሻል ሥራም ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።
ግብርናውን በሜካናይዝድ ማገዝ ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህ ደግሞ ከ80 በላይ ኮምባይነሮችን እና ትራክተሮችን በማሰራጨት የክልሉን የትራክተር ቁጥር ከ1 ሺህ 800 በላይ ማድረስ ተችሏል። የኮምባይነሮች ቁጥር ደግሞ ወደ 35 ማሳደግ መቻሉን ነው የገለጹት። የአማራ ክልል ግብርና ጥራት እና ደኅንነት ባለሥልጣን የዘር ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ጉርሜሳ እጄታ እንዳሉት ደግሞ በ2016/17 የምርት ዘመን 12 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ላይ 275 ሺህ 300 ኩንታል የሚጠጋ ዘር ተሰብስቧል።
ከተሰበሰበው 66 በመቶ ግዢ ተፈጽሟል፤ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 102 ሺህ 765 ኩንታሉ የስንዴ፣ የጤፍ፣ የበቆሎ፣ የአኩሪ አትር፣ የማሽላ ምርጥ ዘር በላብራቶሪ ተፈትሿል፡፡ ከዚህ ውስጥ 74 ሺህ 250 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር እንደኾነ ገልጸዋል። ፍተሻ ከተደረገበት የበቆሎ ዘር ውስጥ 54 ሺህ ኩንታሉ ቀድሞ ለዘር አገልግሎት የሚውል “ቢኤች 661” የተባለ የበቆሎ ዘር ሲኾን 80 በመቶው ለአርሶ አደሮች ተሠራጭቷል።
የክልሉ የምርጥ ዘር አጠቃቀም ሽፋን ከሚታረሰው መሬት ጋር ሲታይ ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። “እናት ዘር” እየተባሉ የሚጠሩት የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የመሳሰሉ ዘሮች እጥረቱ ይበልጥ ጎልቶ ይታያል። የክልሉን የዘር ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በክልሉ የአካባቢውን የአየር ንብረት መሠረት ባደረገ መልኩ የዘር ብዜት የሚካሄድበት ሰፊ ቦታ በማዘጋጀት የማባዛት ሥራው ላይ ትኩረት ማድረግ ቀዳሚው ተግባር ሊኾን እንደሚገባ መክረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሮች በውል የሚያመርቱትን ዘር አስመራች ድርጅቶች ጊዜን እና ወጭን የሚመጥን ግዢ በመፈጸም አምራች አርሶ አደሮችን ማበረታታት እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!