ይቅርታ እና ምህረት ለማን፣ መቼ እና እንዴት?

77

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች ሥልጣን ባለው አካል በእስር የእርማት ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ በይቅርታ ወይም በምህረት ሊለቀቁ የሚችሉበት የሕግ አሠራር አለ፡፡ በዚህ ሕግ መሠረትም ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ሕዝባዊ እና ፖለቲካዊ በዓላትን ምክንያት በማድረግ እስረኞች በምህረት እና በይቅርታ ሲፈቱ ማየት የተለመደ ነው፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ምክትል ረዳት አቃቢ ሕግ ወይዘሮ ትዕግሥት ጣሰው ለአሚኮ በኩር ጋዜጣዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ይቅርታ ጥፋተኝነቱ በሕግ ተረጋግጦ በማረሚያ ቤት የቆየ ታራሚ ይቅርታ የሚደረግለት በቆይታው በሥነ ምግባር መታነጹ እና መጸጸቱ ሲረጋገጥ ነው፡፡ በተጨማሪም የፈጸመው ወንጀል ይቅርታ የማያስከለክል፣ ከእስር ፍርዱም አንድ ሦስተኛ፣ አንድ አራተኛ እና አንድ አምስተኛውን የጨረሰ ሲኾን ነው፡፡

መንግሥት ፍርደኛው ማረሚያ ቤት ከሚቆይ ይልቅ ኅብረተሰቡን ቢቀላቀል ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያበረክታል ብሎ በሚያስብበት ጊዜም ይቅርታ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ ይቅርታ ሊደረግ እንደሚችል በወንጀል ሕጉ ቁጥር 229 ተጠቅሷል፡፡ የይቅርታ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓትን ለመምራት በወጣው አዋጅ ቁጥር 840/2006 መሠረት አንደኛ በሕግ አኳኋን ካልተደነገገ በስተቀር በሕግ የተወሰነ ቅጣት ሥልጣን በተሰጠው አካል በሙሉ ወይም በከፊል በይቅርታ ሊቀር አሊያም ደግሞ በዓይነቱ አነስተኛ ወደኾነ ቅጣት ሊለወጥ ይችላል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ይቅርታ የተሰጠው ታራሚ ከይቅርታው በኋላ ሌላ ወንጀል ፈጽሞ ከተገኘ ቀድሞ የተወሰነበት ፍርድ እንደተጨማሪ የወንጀል ማክበጃ እንደሚያዝ ተደንግጓል፡፡ ሦስተኛው ይቅርታው የወንጀል እንጂ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን (ኀላፊነትን) አያስቀርም፤ ማለትም የሕግ ታራሚው ካሳ እንዲከፍል፣ የመንግሥት ንብረት እንዲመልስ፣ የግለሰብ ሃብት እንዲያስረክብ፣ ተወስኖበት ከኾነ ይቅርታው እነዚህን ጉዳዮች አያካትትም፡፡ ይቅርታ የሚያገኙት በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ብቻ ናቸው፡፡ ተከስሰው በቀረበባቸው ማስረጃ መሠረት በሌሉበት የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው ይቅርታውን አያገኙም፡፡

ምህረት መንግሥት ከይቅርታ በተጨማሪ ምህረትም ይሰጣል፡፡ የምሕረት አሰጣጥ ለማን፤ በማን እና እንዴት በአዋጅ ቁጥር 1089/2010 ላይ ሰፍሯል፡፡ በአዋጁ መሠረት ምህረት ሊያደርግ የሚችለው የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1096/2010 የምህረት አዋጅ እንዴት እንደሚያደርግ እና እንዴት እንደሚሰጥም በዝርዝር ተደንግጓል፡፡

አንድ ሰው ጥፋተኛ ተብሎ በሕግ ቢፈረድበት እንኳን ምሕረት ከተሰጠው ቅጣቱ ይቀራል፡፡ ማለትም ፍርድ ተሰጥቶት ከኾነ ይቀራል፤ በክስ ላይ የነበረ ከኾነ ይቋረጣል፤ ክሱ ካልታየ ደግሞ ክስ አይቀርብበትም፡፡ ምሕረት ፍጹም ነው፡፡ አብዛኞቹ ምህረት የሚሰጣቸው የፖለቲካ ወንጀል ፈጻሚዎች፣ በሕገ መንግሥቱ እና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ወንጀል በመፈጸም፣ በሀገር መክዳት፣ የአመጽ ወንጀሎች እና በሀገር እና በመንግሥት ላይ አመጽ በማስነሳት እና መሰል ድርጊቶችን በመፈጸም ተከሰው ማረሚያ ቤት የቆዩ ታራሚዎች ወይም የሚፈለጉ ሰዎች መንግሥት ያለፈ ጥፋታቸውን ሁሉ ምህረት የሚደርግበት (የሚሰረዝበት) ነው፡፡

ምህረት የተደረገለት አካል ጫካ ገብቶ ከኾነ ምህረት በተደረገለት ጉዳይ ምህረቱን ተቀብሎ ካልገባ እንኳን በሌላ ጊዜ ምህረት በተሰጠበት ወንጀል መልሶ ሊያስከስሰው አይችልም፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ሰው በተደረገለት ምህረት እንደማንኛውም ሰው ንጹህ ተብሎ ቢቆጠርም ሌላ ወንጀል ከሠራ ግን መጀመሪያ የተሰጠው ምህረት አያድነውም፡፡ በ2010 ዓ.ም በወጣው የሕጉ ማስፈጸሚያ አዋጅ ምህረትም ይቅርታም ስለሚደረግባቸው ሥነ ሥርዓቶች ተደንግጓል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28 መሠረት ዘር ማጥፋት፣ ያለ ፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ መውሰድ፣ አስገድዶ ሰውን መሰወር፣ እንዲሁም ኢ-ሰብዓዊ ድብደባ የፈጸመ ታራሚ ግን ይቅርታም ምህረትም አያገኝም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በዘር ማጥፋት ወንጀል ተከስሶ 30 ዓመት ቢጠፋ ይርጋ ሳያግደው በተገኘበት ሰዓት ክስ ይመሠረትበታል፡፡ ኾኖም ግን በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ አንድ የተጠቀሱት ጥፋቶችን ፈጽመው የሞት ቅጣት የተወሰነባቸውን ሰዎች የሀገሪቷ ርዕሰ ብሔር ቅጣቱን ወደ እድሜ ልክ እስራት ሊቀይሩት ይችላል እንጂ ይቅርታ የለውም፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕማሙን ያስባሉ፤ መከራውን ያስታውሳሉ”
Next articleየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ ላበረከተችው አስተዋጽኦ አድናቆቱን ገለጸ።