“ሕማሙን ያስባሉ፤ መከራውን ያስታውሳሉ”

40

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 22/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደል ሳይኖርበት እንደበደለኛ የተቆጠረውን፣ ግፍ ሳይኖርበት እንደግፈኛ የተገፋውን፣ የተዳፋውን፣ መራራ ሐሞት የጠጣውን፣ ጎኑን በጦር የተወጋውን፣ ደሙን ያፈሰሰውን፣ ሥጋውን የቆረሰውን፣ እግር እና እጁ የተቸነከረውን፣ በመስቀል ላይ የተሰቀለውን አምላካቸውን እያሰቡ ያለቅሳሉ፣ ሕማሙን እያሰቡ ያዝናሉ፣ ይተክዛሉ፣ ጫማቸውን ከእግራቸው አውልቀው በባዶ እግራቸው ይጓዛሉ፣ ሥጋቸውን አድክመው ነፍሳቸውን ያበረታሉ፣ መከራውን እያስታወሱ ይሰግዳሉ፡፡

በዚህች ሳምንት ሥጋ ትጨነቃለች፤ በጾም እና በጸሎት ትደክማለች፣ ማጌጥ ይቀራል፤ ተድላ እና ደስታ ይረሳል፤ ይልቅስ ሀዘን እና ለቅሶ ይበዛል፤ ስግደትና ጾም ያይላል እንጂ፡፡ ሊቃውንቱ ልብሰ ተክኗቸውን አውልቀው፣ ወገባቸውን ታጥቀው ግብረ ሕማማቱን ያነብባሉ፣ ሳያቋርጡ ሥርዓቱን ይፈጽማሉ፣ ምዕመናን ጆሮአቸውን ወደ ግብረ ሕማማቱ ያዘነብላሉ፡፡

መከራ የበዛባት፣ ስቃይ የበረታባት፣ ለፍቅር ኃያል መስዋዕትነት የተከፈለባት፣ ዓለምን በእጁ የሚይዘው የተያዘባት፣ የሕይወት ውኃን የሚያጠጣው መራራ ሐሞት የጠጣባት፣ መላእክት ያለ ማቋረጥ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ የሚያመሰግኑት አምላክ የተዘበተበት፣ ልብሱ ብርሃን የኾነ አምላክ የመዘባባች ልብስ የለበሳባት፣ የማይሞተው የሞተባት ሰሙነ ሕማማት በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባሉ ክርስቲያኖች ታላቅ ሳምንት ናት፡፡

በርእሰ አድባራት ወገዳማት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ አንድነት ገዳም የአራቱ ጉባኤያት የምስክር መምህር ርእሰ ሊቃውንት አባ ገበረ ኪዳን ግርማ ሕማም ማለት ስቃይ፣ መከራ ማለት ነው፤ ሰሙነ ሕማማት የሚባለው ደግሞ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ለሰው ብሎ የተቀበላቸውን ሕማማቱን፣ ስቃዩን፣ የምናስብብት ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ ይህን የምናስበው የሃይማኖታችን ነገር የተፈጸመው በዚህ ስለኾነ ነው፡፡ ድኅነታችን የተከናወነው፣ እርግማን የጠፋልን፣ ሞት ድል የተነሳልን፣ መቃብር የተወገደበት፣ ዲያቢሎስ የታሰረበት በክርስቶስ መከራ ነውና ሕማሙን እናስባለን ነው የሚሉት፡፡

ሕማሙን ማሰብ የክርስትና የመጀመሪያውም፤ የመጨረሻውም የሕይወት ዓላማ ነው፡፡ መመኪያችን የክርስቶስ መከራና ሞት ነው፤ ማሕተማችንም የክርስቶስ መከራ ነው፣ ሕጋዊነቱ እንዲረጋገጥ ማሕተም እንደሚደረግበት ሁሉ የክርስቶስ የመኾናችን ምልክት ሕማሙን ስቃዩን መሳተፋችን ነው፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ካልኾነ በስተቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ፣ በሌላ በምንም አልመካም እንደተባለ መስቀሉ መመኪያችን ነው፤ የክርስቲያኖች ኑሯቸው የክርስቶስን ደመ መስቀል፣ ማሕተመ መስቀል፣ ፍቅረ መስቀል ይዞ መኖር ነው፡፡ ያለዚህ የሚኖር ኑሮ የለም፤ ኑሯችን በክርስቶስ ሞት ነው፣ ሕይወታችንም በክርስቶስ ሞት ነው ይላሉ መምህሩ፡፡

መምህሩ ሲናገሩ ሕማሙን ማሰብ ሃይማኖታችን ነው፣ እምነታችን ነው፣ ድኅነታችን ነው፣ ምልክታችን ነው፣ የክርስቶስ የኾኑ ሰዎች በክርስቶስ ሕማም ነው የሚታወቁት ይላሉ፡፡ እርሷ ከእግዚአብሔር የማትለይ፣ እኛን ከእግዚአብሔር የማትነጥል ፍቅር ይህች ናት፤ ይህችም ሕማሙን ማሰብ፣ የክርስቶስን ሞት ማሰብ የማያልቅ ፍቅር ነው፣ የማይነጥፍ የደስታ ምንጭ፣ ክርስቶስ መስቀል ላይ ቤተክርስቲያንን መሥርቷታል፤ ደሙ ሲፈስስ ለእኛ ደስታ ፈልቋል፤ ድኅነት ፈልቆልናል፣ ሕይዎት ፈልቆልናል፤ ነጻነት ፈልቆልናል፤ ዘላለማዊ ሕይዎት ፈልቆልናል፤ እናም ከእግዚአብሔር የማትለይ ፍቅር ይህችን ሕማሙን ማሰብ ነው ይላሉ፡፡

አባ ገብረኪዳን እንደሚሉት ሰው ከእግዚአብሔር መለየት ካልፈለገ የክርስቶስን ሞት መርሳት የለበትም፡፡ የክርስቶስን ሞት የሚያስብ ሰው አይሰርቅም፣ አያመነዝርም፣ አይዋሽም፣ ጣኦት አያመልክም፣ ሥጋውን ወስኖ እና ገትቶ መያዝ ይቻለዋል፡፡ ፍቅር በጎ ነገር ያሠራል፤ የክርስቶስን ፍቅር ማሰብ በመከራ ጊዜ ይታገሳል፤ የማዕዘኗ ራስ ክርስቶስ የኾነላት፣ የተሰናዳች፣ በማሕሌተ መላዕክት የምትታጀብ ቤተክርስቲያን ሕማሙን እንዳንረሳ፣ እንድናስብ የምታደርገን ከፍቅሩ እንዳንነጠል፤ ፍቅሩን እንዳንረሳ፣ ሕማሙም ድኅነትን ያደረገበት መኾኑን እንድናሰብ ነው፡፡

ሰሙነ ሕማማት ሲታሰብ እግዚአብሔር ወደ ምድር የመጣበትን ማሰብ ግድ ይላል። ምን ያክል እንደሚወደን እርግጠኞች የምንኾነው ምን እንዳደረገልን ስናውቅ ነው፣ ሕማሙ የክርስቶስን ውለታ የምናስብበት ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ ሕማሙ ሲታሰብም ራስን በመግታት እና በመወሰን ነው፡፡ ሰውን ሁሉ ከሀጢያት መሳሪያ የሚፈታው እርሱ የታሰረበት፣ ለሰው ፍቅር ሲል መከራ የተቀበለበት፣ በጦር የተወጋበት፣ የተገፋ የተዳፋባት፣ የበዛ መከራ የተቀበለበት በሕማሙ ሳምንት ራስን መግታት ይገባል ነው የሚሉት፡፡

ነጻነት ያለው ክርስቶስ በሰሙነ ሕማማት እንደታሰረ ሁሉ ክርስቲያኖችም በሰሙነ ሕማማት ነጻነት ከተሰጠን በኋላ መስቀል ሳንሳለም፣ ቅዳሴ ተከልክሎ፣ ሰውነታችንን በጾም አስረን፣ ወስነን፣ ገትተን፣ እንኖራለን፤ መስቀል የማንሳለመው ነጻነት ስላልተሰጠ፣ ድኅነት ስላልተደረገ ሳይኾን ነጻነት ያለው አምላክ የታሰረበትን ለማሰብ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሰሙነ ሕማማት ጽዋን፣ ልብሰ ተክኅኖዋን ሁሉ አውጥታ እያዘነች ትሰነብታለች ይላሉ፡፡

ዓለምን በመሐል እጁ እንደ ጽናሕ አንጠልጥሎ፣ እንደ ወርቅ አንከብሎ የያዛትን ጌታ ይዘውታል፤ ቤተክርስቲያንም በሰሙነ ሕማማት መያዙን ለማሰብ ሁሉን ነገር ትይዘዋለች፤ ጌታዬ ተይዟል ብላ ቅዳሴውን ትይዘዋለች፣ ማሕሌቱን ትይዘዋለች፣ ምዕመናን ሥጋቸውን እንዲይዙ፣ እንዲወስኑ ታደርጋለች፣ እስከ ምሽት እንድ ሰዓት ድረስ ምዕመናን እንዲጾሙ፣ እንዲያዝኑ፣ እንዲተክዙ ታደርጋለች ነው የሚሉት፡፡

“በራሳችን ላይ ብንፈርድ ባልተፈረደብንም ነበር” እንደተባለ በሰሙነ ሕማማት ምዕመናን በራሳቸው ላይ እንዲፈርዱ፣ ሥጋቸውን እንዲገስጹ ቤተክርስቲያን ታዛለች፡፡ ሰውነቱን የሚወዳት ካለ ይጣላት፤ ሰውነቱን ዘር አድርጎ፣ መስቀልን እርሻ አድርጎ ይጣል፤ ሰውነቱን ይጣል ማለት እየተነሳ ይውደቅ ማለት አይደለም ዘር እንዲያፈራ እርሻ ላይ ይጣላል፤ ስለዚህ ሰውነቱን የሚወድም ካለ በመከራ መስቀል፤ በሕማማተ መስቀል ይጣላት፤ ሰውነቱን በመስቀል የጣላት ከብራ ያገኛታል፤ ስንዴን ከእርሻ ላይ የጣለ አፍርቶ እንደሚያገኘው ሰውነቱን ወደ ሕማማት የጣለ የክርስቶስን ብርሃን ለብሳ ያገኛታል ነው የሚሉት፡፡ በሰሙነ ሕማማት መስቀል አይሳለምም፤ ይሄውም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ ሰላሙን ሰጥቶ ያረጋጋቸው እሁድ በትንሳኤው ስለኾነ ያንን ለማሰብ ነው፡፡

ለሰው ሁሉ ሕይዎትን የሚያድለውን ጌታን ሐሞትን፣ ከርቤን፣ መራራ ሞትን አጠጡት፤ ይሄን ለማሰብም ምዕመናን በሰሙነ ሕማማት ለአፋቸው ምሬት እስኪሰማቸው ድረስ እየጾሙ መረራ ሐሞት የተቀበለውን ጌታን ያስባሉ፡፡ ሳይሞት ማዳን ይቻለው ነበር፣ እርሱ ግን የሰውን አካል ለብሶ ተበድሎ ሳለ ሊክስ፣ የሰውን ልጅ ከሞት ሞት ሊያድን፣ ነጻ ሊያወጣ መጣ፡፡ የፀሐይ ብርሃን ከላይ ከክበቡ ሳይለይ ወደ ምድር እንደሚወርደው ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንበሩ ሳይጎድል መጥቶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተጸነሰ፣ አካላችንን ለበሰ፣ ተዋሐደ፣ ባሕሪ አደረገው፤ ለምን ሰው ስለበደለ፣ ካሳ ማቅረብ ስለነበረበት እዳ የሌለበት ክርስቶስ ከንጽሒት ድንግል ማርያም ሥጋን ለብሶ፣ በሰው አካል ካሳውን አቅርቦ ራሱ ታቀረን ይላሉ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን የከፈለውን ውድ ዋጋ ሲገልጹ፡፡

አባ ገብረኪዳን ሲናገሩ በመብል ጠፍተን ነበር ተራበልን፣ መብል አድርጎ ሥጋውን ሰጠን፣ መጠጥ አድርጎ ደሙን ሰጠን፣ እግራችን ወደ በለስ ሄዶ ነበረ እግሩ ተቸንክሮ ወደዚህ ዛፍ አትሂዱ ተብሎ የተነገረንን ትዕዛዝ ለተላለፍንበት ካሳ ካሰልን፣ ሴቲቱ እጹ አስጎምጅቷት ነበር፤ በዓይኗ ለሰራችው በደል ክርስቶስም ዓይኖቹ ደም ለብሰው፣ ግርማ አይሁድን እያየ በጲላጦስ ፊት ቆሞ፣ አይሁድ እያስፈራሩት አይሁድን እያየ ካሳ ክሶልናል፤ በለስን በእጃችን ቆርጠን ለበደልነው በደል እጆቹ ተቸነከሩ፤ በለስን ለበላንበት አፍ ሐሞት ጠጥቶ ካሳ ካሰን፣ መራራ ሞትን አስቀረልን፣ ለእኛም ጣዕመ መንግሥተ ሰማያትን ሰጠን፣ እሾህ ይብቀልብን የሚል እርግማን ነበረብን የእሾህ አክሊል በራሱ ላይ ደፋ፣ እርሱ የእሾህ አክሊል ሲደፋ ከእኛ ላይ የሐጥያት እሾህ ተነቀለልን፣ በሞቱ ሞትን አሸነፈልን ሕማማትን የምናስበውም ይሄን ሁሉ ለማሰብ ነው ብለዋል፡፡

በሰሙነ ሕማማት ፍትሐት አይደረግም፤ “ከሀጢያት የሚፈታውን አሠሩት” እንደተባለ ያን ለማሰብ ነጻነት ሳለን በሰሞነ ሕማማት ፍትሐት አይደረግም ይላሉ፡፡ እስከ ትንሳኤው የሚሞት ሰው ቢኖር ለሁሉም ተጠቅልሎ በዕለተ ሆሳዕና ፍትሐት ይደረግለታል፡፡ በሰሙነ ሕማማት 40 ቀን የሞላቸው ወንዶች፣ 80 ቀን የሞላቸው ሴቶች ክርስትና አይነሱም፣ ቀኑ እንዳለፈ አይቆጠርባቸውም፣ በዕለተ ትንሳኤው ክርስትና ይነሳሉ ነው የሚሉት፡፡

ቀናቱም እሁድ ሆሳዕና፣ ሰኞ አንጽሆተ ቤተ መቅደስ ቤተ መቅደስን ላነጻበት ቀን መታሰቢያ፣ ማክሰኞ የትምህርት ቀን ይባላል፤ ጌታ ሰፊ ትምህርት ያስተማረበት ቀን ነው፤ ረቡዕ ምክረ አይሁድ ይሰኛል፤ አይሁዳውያን የተማከሩበት ቀን፤ ሐሙስ ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፤ ጌታም አብዝቶ የጸለየበት፣ ዝቅ ብሎ እግር ያጠበበት ነው፤ ትሕትናውን የገለጠበት፣ ከዋሐርያት ጋርም ራት ላይ የተገኘበት፣ አርብ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት፣ ቅዳሜ በከርሰ መቃብር የዋለባት ናት፣ እሁድ ከሙታን ተለይቶ የተነሳባት ቀን ናት፡፡

መምህሩ እንደሚሉት በሰሙነ ሕማማት ተድላ ደስታ ያደረገ፣ ጌጥ ያጌጠ ደስ ያለው፣ መብል መጠጥን አብዝቶ የሚደሰት ሰው ቁጥሩ ከአይሁድ እና ከይሁዳ ጋር ነው፡፡ በሰሙነ ሕማማት መከራውን በማሰብ፣ ቤተክርስቲያን በመዋል በማደር፣ ግብረ ሕማማትን በመስማት፣ ሥጋዊ ነገርን ትቶ ይቆያል ነው የሚሉት፡፡ የቻለ ከሐሙስ ጀምሮ፣ ካልኾነ ግን ከአርብ ጀምሮ ጌታ እስኪነሳበት ጊዜ ማክፈል ይገባልም ይላሉ፡፡

አባ ገብረኪዳን ሲናገሩ ፋሲካ ማለት መሻገር፣ ማለፍ ማለት ነው፡፡ ማለፍ የተባለበትም እስራኤላውያንን ሞቱ ስላለፋቸው ነው፣ ሞተ በኩር በጉን እያየ ስላለፋቸው ነው፣ እኛንም የክርስቶስን ደም እያየ ሞት አልፎን ይሄዳል፤ መሻገርም ከግብጽ ወደ ከነዓን ተሻግረዋል፤ እኛንም ከሲኦል ወደገነት ስላሻገረን ክርስቶስ ፋሲካችን አሻጋሪያችን ነው። እናም በዚህ ሰዓት ራስን መለወጥ፣ ከክፋት መውጣት፣ ከነውር መውጣት፣ ከዓድማ ፣ ከዘረኝነት፣ ከመለያየት፣ ከዝሙት፣ ከተንኮል፣ ከነፍስ መግደል፣ ከነገር ሥራ፣ ሰዎችን ከማሳቃየት፣ ከቂም ከበቀል ያልተሻገረ ሰው ፋሲካን አከበርኩ ማለት አይቻለውም ይላሉ፡፡

ከሀጢያት ወደ ጽድቅ፣ ከክህደት ወደ ሃይማኖት፣ ከመለያየት ወደ አንድነት፣ ከጠብ ከክርክር ወደ ፍቅር፣ ከሞት ወደ ሕይዎት እንድንሻገር፣ ኢትዮጵያም ወደ ሰላም እንድትሻገር፣ መለያየት እንዲጠፋ፣ ፍቅር እንዲነግስ፣ በሀገር ያለው ሁከት፣ ዘረኝነት እና ክፋት እንዲጠፋ፣ ፍቅር አንድነትን አስበን፣ በመታረቅ በሰላም ኾኖ ማሰብ ይገባል ነው የሚሉት፡፡

ሰሙነ ሕማማት ደርሳለችና ክርስቲያኞች ሕማሙን እያሰቡት፣ መከራውን እያስታወሱት፣ ትንሳኤውንም በተስፋ እየጠበቁት ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰሜን ጎጃም ኮማንድፖስት በአዴት ከተማ በጽንፈኞች ታግቶ የነበረ የሰባት ዓመት ህጻን አስለቀቀ።
Next articleይቅርታ እና ምህረት ለማን፣ መቼ እና እንዴት?