የሰሜን ጎጃም ኮማንድፖስት በአዴት ከተማ በጽንፈኞች ታግቶ የነበረ የሰባት ዓመት ህጻን አስለቀቀ።

22

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሚያዝያ 11/2016 ዓ.ም በአዴት ከተማ አዩ መሐመድ የሚባል የሰባት ዓመት ህጻን አግቶ በመውሰድ ገንዘብ ካልሰጡት እንደሚገድለው በመዛት ከህጻኑ ቤተሰቦች ጋር ሲደራደር ቆይቷል ተብሏል። በአካባቢው የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ባደረገው የተጠናከረ የመረጃ እና የክትትል ሥራ ከ9 ቀናት በኋላ ህጻኑ ታግቶ ከነበረበት ቦታ ከነአጋቾቹ በቁጥጥር ሥር በማዋል ህጻኑን ለቤተሰቦቹ አስረክቧል፡፡

ሠራዊቱ በእገታ ወንጀል ላይ የተሰማሩትን ሦስት የጽንፈኛው ቡድን አባላትን በሕግ አግባብ እንዲጠየቁ በአካባቢው ለሚገኝ የፀጥታ አካል አስረክበዋል፡፡ የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ዓለሜ ታደለ ጽንፈኛው ቡድን ሕገ ወጥ ድርጊቶች እና የወንጀል ተግባራት፣ ስርቆት፣ የተደራጀ ዘረፋ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በኅብረተሰቡ ላይ ሲፈጽም መቆየቱን አስታውሰው ሠራዊቱ በወሰደው የማያዳግም እርምጃ አከርካሪው በመሰበሩ ሕዝቡ ወደ ልማቱ ተመልሷል ብለዋል።

በቀጣይም ተገቢውን ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም አጥፊዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ እና ለሕግ የማቅረብ ሥራዎችን ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በጋራ በመስራት የሕዝቡን ሰላም እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡ ሕዝቡ የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ጥፋተኞችን ለሕግ አካል አሳልፎ በመስጠት እያደረገ ላለው መልካም ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ሰራዊቱ እነዚህን እና መሰል የጥፋት ተግባራት ላይ ተሰማርተው የማኅበረሰቡን ሰላም ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና ቡድኖችን ከክልል የፀጥታ አካላት እና ከሕዝቡ ጋር በመኾን እርምጃ የመውሰድ እና ለሕግ የማቅረብ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

መረጃው የሰሜን ጎጃም ኮማንድፖስት ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን ለማጠናከር የሚያስችል 165 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አገኘች።
Next article“ሕማሙን ያስባሉ፤ መከራውን ያስታውሳሉ”