195 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት መቻሉን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡

21

ደሴ: ሚያዚያ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ባለፈው በጀት ዓመት ገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች በመተካት 195 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል፡፡ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ በከተማዋ ካሉ ባለሃብቶች እና አጋር አካላት ጋር በኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ መድረክ በደሴ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩ ባለሃብቶች ከተማ አሥተዳደሩ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት በትክክል ሀገርን እንደሚያሻግር በማመን ያሉብንን ችግሮች ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ አለባቸው ሰይድ በደሴ ከተማ በበጀት ዓመቱ ለ160 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡ ባለሃብቶቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ከ40 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥሩም ገልጸዋል።

አቶ አለባቸው ከዚህ ቀደም ለኢንዱስትሪ ልማት መሬት ወስደው ግንባታ ያላጠናቀቁ፣ ግንባታ አጠናቀው በፍጥነት ወደ ሥራ ያልገቡ እንዲሁም የተረከቡትን መሬት ከታለመለት ዓላማ ውጭ ያዋሉ 17 ባለሃብቶች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንም ጠቅሰዋል። የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባለፈው ዓመት ብቻ ለረጅም ግዜ ምርት አቁመው የነበሩ 255 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እና አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት ከ63 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ ክልሉ ችግር ውስጥም ኾኖ ገቢ ምርትን በሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች በመተካት 195 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት መቻሉን ገልጸዋል። በተጨማሪም 30 የአምራች ኢንዱስትሪዎች እና 9 የአበባ ልማት ድርጅቶች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ 78 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- መስዑድ ጀማል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየ12ኛ ክፍል ፈተና የሚሰጥበት ቀን ይፋ ኾነ።
Next articleኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማትን ለማጠናከር የሚያስችል 165 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አገኘች።