
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በዛሬው እለት በኬንያ እየተካሄደ ባለው ዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጉባኤ መልእክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ በፈተናዎች ሁሉ የተሻገረ ያለመበገር ፅናት የምጣኔ ሃብት መረጋጋትን እና ምርታማነትን ባስቀደሙት በመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎቿ ማሳያነት ይገለጣል ብለዋል።
በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በሚመራው ሥራ ምክክር እና እርቅ የሰላም ፍላጎታችን እና ተምኔታችን ማጠንጠኛ ናቸው። ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ ብሎም ወጣቶችን በማብቃት ኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን አዳዲስ ሥራዎችን ለመፍጠር አልማለች ነው ያሉት።
አረንጓዴ ዓሻራ በመሰሉ ንቅናቄዎች ኃይል ለሁሉም ማዳረስ፣ የዲጂታል ሽግግር እና የተፈጥሮ ከባቢን የመንከባከብ ተግባራትን ለመከወንም ትኩረት ትሰጣለች። ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ለአሕጉሩ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ ታደርጋለች ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!