
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የብሔራዊ ኢ-ኮሜርስ ስትራቴጂ ሰነድ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ በንግግራቸው ሀገራዊ የልማት ፕሮግራሞችን በስኬት ለመፈጸም፣ ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነታችንን ከፍ ለማድረግ ኢ-ኮሜርስን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ኢ-ኮሜርስ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወትም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመተግበር እና ኢ-ኮሜርስን በማላመድ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚጠይቅም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ኢ-ኮሜርስ የንግድ ተቋማት ጊዜ እና ቦታ ሳይገድባቸው ከደንበኞቻቸው የሚገናኙበት እና የሀገር ውስጥ ንግድ እንዲሳለጥ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ኢ-ኮሜርስ የዲጂታል ኢትዮጵያን ስትራቴጂ እውን ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር) እና ሌሎች ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የሚመለከታቸው የክልሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ነጋዴዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!