
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ ከ25 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት ማሰባሰብ መቻሉም ተገልጿል። ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የተጀመረውን የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ሕዝባዊ ንቅናቄ ግለቱን ጠብቆ ማስቀጠል እንደሚገባ በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ ጠቁመዋል።
ትምህርት የሁሉም መሠረት እንደኾነ ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ በትምህርት ሥርዓቱ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚኾን መሠረት ለመጣል ጠንክሮ መሥራት ይገባል ብለዋል። በዚህም የትምህርት ስብራቱን ለማከም የሚያስችል አሻራ መጣል እና ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ አሁን በትምህርት ዘርፉ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተጀመሩ ሥራዎችን የበለጠ ከፍ ለማድረግ በተነሳሽነት እና በቁርጠኝነት እንዲሠሩም አሳስበዋል።
በትምህርት ዘርፉ የተካሄደው የትምህርት ለትውልድ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻል ንቅናቄ ኅብረተሰቡ በትምህርት ላይ ያለውን የባለቤትነት ሚና በትክክል ያረጋገጠ እና ለሌሎች ሴክተሮችም ተሞክሮ መኾን እንደሚችል በመድረኩ ተነስቷል። የትምህርት ሚኒስቴር ሱፐርቪዥን ቡድን በክልሎች ያደረገው ምልከታ ሪፖርትም በመድረኩ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
እንደ ትምህርት ሚኒስቴር መረጃ የሱፐርቪዥኑ ዋና ዓላማ መደጋገፍ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደኾነም ተገልጿል፡፡ በሱፐርቪዥኑ የታዩ መልካም አፈጻጸሞችን ማጠናከር እንዲሁም የታዩ ክፍተቶችን ደግሞ በቀጣይ በዕቅድ አካቶ ለመሥራት እድል የሚፈጥር ነውም ተብሏል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!