ኢትዮጵያ በሠራችው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበሯ ተገለጸ።

14

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር አብዱ ያሲን ኢትዮጵያ በሠራችው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊጣሉባት የነበሩ ማዕቀቦችን ማክሸፏን ተናግረዋል።

አምባሳደር አብዱ ያሲን ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 15 ጊዜ አጀንዳ ኾና ቀርባለች ብለዋል። ይሁን እንጅ በሠራችው ጠንካራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ ሊጣሉ የታሰቡ ማዕቀቦችን ማክሸፍ ችላለች ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ እውነቱን እንዲያውቅ የተሰሩ የሕዝብ ለሕዝብ መድረኮች ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አመልክተዋል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲውን አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳደግ ኢትዮጵያ ከበርካታ የዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር የእህትማማች ስምምነት መፈረሟን ገልጸው የተፈረሙ ስምምነቶችም ለሀገራዊ አንድነት፣ ለቀጣናው ትስስር እና ለሁለትዮሽ ግንኙነት ማደግ እገዛ እያበረከቱ መኾኑን አስታውቀዋል።

ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በአንድ ሀገር ውስጥ የሁሉም ዜጋ ሥራ ነው ያሉት አምባሳደር አብዱ የተለያዩ የማኅበረሰብ አባላት እና ተወካዮች ሀገራቸውን በሚገባና በሚችሉት ልክ ማስተዋወቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በትምህርት ዘርፍም ከሌሎች ሀገራት ጋር ጥሩ ትስስር እየተፈጠረ በመኾኑ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ውጤት እያመጡ ነው። አማርኛ በቻይና ዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ነው። በቀጣይም ሌሎች ቋንቋዎችን እንዲያስተምሩ እየተመካከርን በመኾኑ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ በትልቁ የማስተዋወቅ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

ኢትዮጵያም ለጎረቤት ሀገራት በርካታ የትምህርት እድል ሰጥታለች ያሉት አምባሳደር አብዱ በያዝነው ዓመት ለጎረቤት ሀገራት ከ850 በላይ የትምህርት እድል መስጠቷን አንስተዋል። የትምህርት ዕድል ያገኙት የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ስለኢትዮጵያ መልካም አመለካከት እንዲኖራቸው ያደርጋልም ብለዋል።

እንደ ኢፕድ ዘገባ በቀጣይ ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰሞነ ህማማቱን ስናስብ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ያለችውን ሀገራችን ኢትዮጵያን በማሰብ ሊኾን ይገባል” የሃይማኖት አባት
Next articleበትምህርት ለትውልድ ሕዝባዊ ንቅናቄ ከ25 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት ማሰባሰብ መቻሉ ተገለጸ፡፡