“ሰሞነ ህማማቱን ስናስብ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ያለችውን ሀገራችን ኢትዮጵያን በማሰብ ሊኾን ይገባል” የሃይማኖት አባት

15

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አማኞች ዘንድ የዐብይ ጾም የመጨረሻ ሳምንት የኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ህማማት የሚታሰብበት ጊዜ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቢ ሀዲስ ነቅዓ ጥበብ አባቡ ሰሞነ ህማማት ሲባል ከእለተ ሆሳዕና ሰርክ እስከ ትንሳዔ ሌሊት ያለውን ጊዜ እና ቀናት የሚያመለክት መኾኑን ይናገራሉ፡፡

ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል ህማማት እና መከራን እስከ ሞት ተቀብሏል ብለዋል፡፡

ሰሞነ ህማማት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ ሲል የተቀበላቸውን መከራዎች የምናስብበት እና ስለፍጹም ፍቅሩ የምንማርበት ወቅት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ በማሰብ ስለበደላቸው እና መተላለፋቸው ምህረት እንዲያገኙ እጅግ የሚያዝኑበት እና የሚሰግዱበት ሳምንት ነው።

አርብ የመከራ ምሳሌ ናት ያሉት መጋቢ ሀዲስ ነቅዓ ጥበብ ከአርብ በሁዋላ እሁድ መምጣቱ የማይቀር ነውና ስቅለቱ በትንሳዔው ይከበራል ብለዋል፡፡

“ሰሞነ ህማማቱን ስናስብ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ያለችውን ሀገራችን ኢትዮጵያን በማሰብ ሊኾን ይገባል” ብለዋል፡፡

ሀገራችን የመከራዋ አርብ አልፎ የትንሳዔዋን እሁድ ለማየት እንችል ዘንድ ሁላችንም ክርስቶስ እንዳስተማረን በፍቅር፣ በይቅርታ እና በትህትና ስለአንዲት ሀገራችን በአንድነት ወደ ፈጣሪ ልንማጸን ይገባል ሲሉ አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::

ዘጋቢ፡- ሥነ-ጊዮርጊስ ከበደ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ምስጋና አቀረቡ።
Next articleኢትዮጵያ በሠራችው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበሯ ተገለጸ።