
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የመካከለኛ ዘመን የጤና ዘርፍ የልማት እና ኢንቨስትመንት እቅድ ማስጀመሪያ ለባለድርሻ አካላት ትውውቅ አድርጓል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ አብዱልከሪም መንግሥቱ ማከም እና መከላከል ላይ ትኩረቱን ያደረገው የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል። ፖሊሲው ሁሉን አቀፍ የጤና ፍትሐዊ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ እንደኾነ ገልጸዋል።
በተለይም የእናቶችን፣ ሕጻናትን እና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት፣ ተላላፊ በሽታዎች፣ በአዲስ ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞች ትኩረት መደረጉን አንስተዋል። ፖሊሲውን ለማስፈጸም በዋናነት የተለያዩ ስትራቴጅዎች እና መርሐ ግብሮች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ስትራቴጅውን ለማስፈጸም ደግሞ የሦስት ዓመት እቅድ ማዘጋጀት አስፈልጓል ነው ያሉት።
እቅዱ የጤና አገልግሎቱን ፍትሐዊ ተደራሽነት እና ዘላቂነት ማረጋገጥ ዓላማ ያደረገ ነው። የእናቶችን፣ ሕጻናትን፣ የጨቅላ ሕጻናትን ሕመም እና ሞት መቀነስ ሌላው ግብ ኾኖ መቀመጡን አንስተዋል። ተላላፊ እና ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎችን መከላከል እና መቆጣጠር ሌላው የትኩረት አቅጣጫ መደረጉን ነው የገለጹት።
የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበበራከቱ መምጣታቸውን ያነሱት ኀላፊው ሊከሰቱ የሚችሉ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ዝግጁነት እና ምላሽ አሰጣጥ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መኾናቸውንም ነው የገለጹት።
የእቅዱን ስኬታማነት ለማረጋገጥ ከተለመደው አሠራር በመውጣት አዳዲስ አሠራሮችን ማመንጨት፣ አሠራሮችን ዲጅታላይዝ ማድረግ፣ የመፈጸም እና ማስፈጸም አቅም ማሳደግ፣ የታቀደውን እቅድ በተግባር ላይ ማዋል ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች እንደኾኑ ጠቅሰዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ ባለድርሻ አካላት ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እንዲሠሩ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የእቅድ ዝግጅት ክትትል እና ግምገማ ተተኪ ዳይሬክተር ሲስተር ሄለን ተሰማ በበኩላቸው እቅዱ የሀገሪቱን የጤና ፖሊሲ፣ ሀገሪቱ የፈረመቻቸውን የዘላቂ ልማት ግብ እና ክልሉ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ተዘጋጅቷል። ለዚህም ደግሞ ከተቋማት እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለመተግበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም በባለቤትነት እንዲያግዝ ጠይቀዋል።
እቅዱ ግብን እንዲመታ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ሁለት ሺህ የሚኾኑ የጤና ባለሙያዎችን ለመቅጠር ታቅዷል። ይህም የሠራተኛውን ቁጥር ወደ 79 ሺህ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
እቅዱ ከ2016 ዓ.ም እስከ 2018 ዓ.ም የሚተገበርም ይኾናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!