“በጸጥታ ችግር ተዘግተው ከነበሩ ትምህርት ቤቶች መካከል ከ360 በላይ የሚኾኑት ተከፍተዋል” ትምህርት ቢሮ

24

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ተፈጥሮ በቆየው የጸጥታ ችግር ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው ቆይተዋል። መምህራን የተማሪዎችን መምጣት በተስፋ ሲጠብቁ ከርመዋል፡፡ በዓመቱ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር እቅድ ይዞ የነበረው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እቅዱ በተፈለገው ልክ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር መሻሻል በማሳየቱ ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱ ነው፡፡ ተማሪዎች እና መምህራንም እውቀትን ለመቀበል እና ለመስጠት መገናኘት ጀምረዋል፡፡ ለወራት ትምህርት ቤታቸውን የናፈቁ ተማሪዎችም በደስታ ወደ ትምህርት ቤቶቻው እሄዱ ነው፡፡

ስሟን ያልጠቅስነው በምሥራቅ ጎጃም ዞን የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ ትምህርት ቤት ሳይከፈት በመቆየቱ ብዙ ጉዳት ደርሶብናል፤ ተጨናንቀናል፣ ሌሎች እየተማሩ እኛ ሳንማር ስለቀረን የሥነ ልቦና ችግር ደርሶብናል ነው ያለችው፡፡ ዘግይቶም ቢኾን ስለተከፈተ ደስ ብሎኛል፤ ነገር ግን ገና ከተከፈተ ሦስት ሳምንታት ብቻ ነው ብላለች፡፡

ለተማሪ በትምህርት ወቅት ከቤት መዋል ጫናው ከፍተኛ ነው ያለችው ተማሪ ትምህርት ቤታችን በመከፈቱ የተሰማኝ ደስታ ልገልጸው አልችልም፣ ከጓደኞቼ፣ ከመምህራን ጋር በመገናኘቴ ደስተኛ ነኝ ብላለች፡፡

እንኳን ትምህርት ጀመርን እንጂ የማካካሻ ትምህርቱን ለመውሰድ ፈቃደኞች ነን፣ ሰላም ከኾነ በቀሪ ጉዜያት እናካክሰዋለን፣ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተወዳደሪ እንድንኾን ሰላም እንዲኾን እንፈልጋለን፤ ሁሉም ሰላም እንዲያደርግልን እንፈልጋለን ነው ያለችው፡፡

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደግሰው መለሰ በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በትምህርት ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ተፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ በዓመቱ መጀመሪያ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅደው 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎችን ብቻ መመዝገባቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይኽም የእቅዱን 58 በመቶ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ከ3 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ዝግ እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡ በኋላ ላይ በተደረጉ ውይይቶች እና በተሠሩ ሥራዎች ለውጥ እንዲመጣ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል፡፡

ትምህርት የጀመሩ ትምህርት ቤቶችን ማስቀጠል በሚቻልበት እና ትምህርት ያልጀመሩትንም ለማስጀመር በየደጃው ከሚገኙ መሪዎች ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በተደረገው ውይይትም ለውጦች መታየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ 364 ትምህርት ቤቶችም ተከፍተዋል ነው ያሉት፡፡ ዘግይተው የጀመሩ ትምህርት ቤቶች ያባከኑትን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ የሚያስችል አሠራር መውረዱንም ተናግረዋል፡፡ የባከነውን ጊዜ በሚያካክስ መልኩ የትምህርት ሥርዓቱን ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡

ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ የማካካሻ ትምህርት እየተሠጠ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ተማሪዎች ከአቻዎቻቸው ወደ ኋላ እንዳይቀሩ፣ በግጭት ምክንያት የተፈጠረው መዘግየት በቀጣይ ሕይወታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያደርስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ከተከፈቱ በኋላ ተመልሰው የተዘጉ እና እስካሁን ድረስ ያልተከፈቱ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ እተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሥራ ከጊዜ ጋር በእጅጉ የተገናኘ ነው ያሉት ኀላፊው እያንዳንዷ የምትባክን ቀን ከእያንዳንዱ ተማሪ የሚባክን እድሜ ላይ የሚቀነስ ነው ብለዋል፡፡ የሚባክን የትምህርት ጊዜ በተማሪዎች፣ በክልሉ እና በሀገር ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ በበመረዳት ሁሉም አካል የመማር ማስተማሩ ሥራ እንዲቀጥል የድርሻውን መወጣት ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

የትምህርት ጥራትም ትኩረት እንደተደረገበት ነው የተናገሩት፡፡ መምህራን ብቁ ትውልድ ለመፍጠር መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡

የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ሁሉም ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት፡፡ የተከፈቱ ትምህርት ቤቶችም እንዳይዘጉ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት፡፡ ዋጋ እየከፈሉ ትምህርት ቤቶች እንዳይዘጉ የሚያደርጉ መምህራን እና መሪዎች መኖራቸውን የተናገሩት ኀላፊው ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ትምህርት ቤቶችን ለማስከፈት ተነሳሽነት የሌላቸው መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ከተከፈቱም እንዳይዘጉ ጥረት ማድረግ አለበት ነው ያሉት፡፡ የተማሪዎች ምዘና የተማሪዎችን ዝግጁነት ታሳቢ በማድረግ በዙር እንዲሰጥ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ ለመመዘን ተብሎ ተማሪዎችን ላልተገባ ጉዳት የሚዳርግ ሥራ አንሰራም ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በደሴ ከተማ የተሰሩ የልማት ሥራዎች በችግር ውስጥም ኾኖ አመርቂ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ማሳያ ናቸው” አደም ፋራህ
Next articleየማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል የተቀመጡ ግቦች እንዲሳኩ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ።