
ደሴ: ሚያዚያ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በደሴ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎች የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በደሴ ከተማ በመንግሥት እና በሕዝብ ተሳትፎ የተሠሩ የኮሪደር ልማቶች በፌደራል እና በክልል ከፍተኛ የመንግሥት ኀላፊዎች መጎብኘታቸውን የገለጹት የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ናቸው። የከተማዋን ሁለንተናዊ ገጽታ የሚቀይሩ የአስፋልት መንገዶች፣ የመናኽሪያ ግንባታ እና የከተማ ማስዋብ ሥራዎች የጉብኝቱ አካል ነበሩ ብለዋል።
የሥራ ኀላፊዎቹ በተመለከቷቸው የልማት ሥራዎች ተደስተዋል ያሉት ከንቲባው የከተማ አስተዳደሩን እና ሕዝቡን ማመስገናቸውንም ተናግረዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚደንት አደም ፋራህ “በደሴ ከተማ የተሰሩ የልማት ሥራዎች በችግር ውስጥም ኾኖ አመርቂ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ማሳያ ናቸው” ብለዋል።
ደሴ ከተማ ሰላሟን ጠብቃ በልማት ሥራዎቿ ተምሳሌት መኾን ችላለች ያሉት አቶ አደም ፍራህ የአማራ ክልልን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው የደሴ ከተማ የመሠረተ ልማት ሥራዎች አበረታች ውጤት የተመዘገባቸው መኾናቸውን ገልጸዋል። የልማት ሥራዎቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉም የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዓሊ ይመር
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!