
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ደመናዎች የሚታዘዙለት፣ ሰማያት የማይችሉት፣ ዓለማት የማይወስኑት፣ ቁጥር ሥፍር የሌላቸው መላእክት በቀኝ በግራው፣ በፊት በኋላው የሚሰግዱለት፣ ያለ ማቋረጥ ቅዱስ ቅዱስ የሚሉት፣ ብርሃናት የሚያመሰግኑት አምላክ መጥቷልና ፍጥረታት እልል አሉለት፣ ዘንባባ እየዘነጠፉ ለክብሩ አነጠፉለት፣ ሕጻናት ዘመሩለት፣ አረጋውያን ለክብሩ ምስጋና አቀረቡለት፡፡
ምድር በደስታ ተመላች፣ በምስጋና ተናወጠች፣ በውዳሴ ተጨነቀች፤ በአምላኳ ማዕዛ ታወደች፤ በግርማው ተከለለች፤ በቅዱሳን እግሮቹ ተረገጠች፤ በቅዱሳን እጆቹ ተባረከች፣ ተስምቶ በማይጠገብ አንደበቱ ድምጽን ሰማች፤ የታደለች ጎዳና አምላክ ተመላለሰባት፤ የታደለች ምድር አምላክ ሰው ኾኖ ታየባት፣ የታደሉ ፍጥረታት አምላካቸውን አዩት፤ በጎዳናዎች ተቀበሉት፤ በተጓዘበት ተከተሉት፣ እያዩት አመሰገኑት፤ እያዩት ለመኑት፤ እያዩት የልባቸውን መሻት ነገሩት፤ ቸርነቱን ያደርግ ዘንድ፣ ድኅነቱንም ይሰጥ ዘንድ ተማጸኑት፡፡
ሰዎች የሚንቋት ፍጥረት አምላኳን ተሸከመች፣ የከበረውን ይዛለችና ተከበረች፣ በተነጠፉ ጎዳናዎች ተጓዘች፣ እልልታ እና ምስጋና በበዛባቸው ጎዳናዎች ተረማመደች፤ እርሷ የተሸከመችው ያማሩ ሰረገላዎች ከተሸከሟቸው፣ ከጎዳና ጎዳና ካመላሷቸው፣ በወርቅ ከተንቆጠቆጡት፣ በአልማዝ ካጌጡት፣ ለእግራቸው መረገጫ ወርቅ ከተጫሙት ነገሥታት ሁሉ ይልቃል፡፡ በሠረገላዎች የታዩት፤ በወርቅ እና በአልማዝ ያሸበረቁት ነገሥታት ሁሉ እንደጤዛ ይረግፋሉ፤ እንደ ጥላ ያልፋሉ፤ እንደሸክላ ይሰበራሉ፤ በዘመን ይወሰናሉ፣ በግዛት ይከለላሉ፤ እርሱ ግን ዘመን አይለካለትም፤ ቀን አይቆጠርለትም፤ ወሰን አይወሰንለትም ነበረ፣ አለ ፣ ይኖራል እንጂ፡፡
ፍጥረታት ሁሉ የሰማዩን መድኃኒታቸውን፣ የሰማዩን ጌታቸውን፣ የማይጠፋ ብርሃናቸውን፣ የማያልፍ አባታቸውን፣ የማያንቀላፋ እረኛቸውን፣ ዘመኑ የማያልፍ ንጉሣቸውን ሆሳዕና በአርያም እያሉ አመሰገኑት፡፡ መዳንን ይሻሉና ጌታ ኾይ አሁን አድን እያሉ ተማጸኑት፤ በሰማይ ያለህ መድኃኒት ኾይ አድነን አሉት፡፡ እርሱም መድኃኒት ነውና ያድናቸዋል፤ ይባርካቸዋል፣ ይቀድሳቸዋል፡፡
አበው ሆሳዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው፡፡ መድኃኒት የተባለውም ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኔዓለም ነው፡፡ ሆሳዕና በአርያም ማለትም በሰማይ ያለ መድኃኒት ማለት ነው፡፡ ከምድር ሁሉ መድኃኒቶች ይልቃል፤ እንደ እርሱ አይነት መድኃኒት የለም፡፡ የሰው ልጅ በስጋም በነፍስም በሽተኛ ነበር፡፡ ከሰማይ ያለው መድኃኒት ግን ከሰማይ መጣ፡፡ መጥቶም አዳነው፡፡ እርሱ የዓለም መድኃኒት ነው፡፡ ዓለምም የሚታየውና የማይታየው ነው፤ የሚለከውና የማይለከው ነው፣ በሰዎች አዕምሮ የታሰበው እና የማይታሰበው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየረር መካነ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያት የመጻሕፍት መምህር መላከ ታቦር ኃይለ ኢየሱስ ፈንታሁን ሆሳዕና ማለት ቅዱስ ዳዊት አቤቱ አሁን አድን እንዳለ መድኃኒት ነው፣ አሁን አድን ማለት ነው ይላሉ፡፡ ጌታ ከደብረ ዘይት ተራራ ሥር ተነስቶ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፡፡
የኔታ እንደነገሩኝ ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደሱ አሥራ ስድስት ምዕራፋት አሉ፤ አሥራ አራቱን ምዕራፋት በእግሩ ሄዳቸው፣ ሁለቱን ምዕራፋት በእናቲቱ አሕያ ሄደ፡፡ ቤተ መቅደሱን ደግሞ በውርንጭላይቱ ሦስት ጊዜ ዞረው፣ ይሄም ዑደተ ሆሳዕና ይባላል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ ሕጻናት፣ ሽማግሌዎች ልብሳቸውን እየጎዘጎዙ፣ ዘንባባ እያነጠፉ ሆሳዕና በአርያም ለወልደ ዳዊት፣ ለዳዊት ልጅ በአርያም መድኃኒት መባል ይገባዋል እያሉ ተቀበሉት፡፡
በዕለተ ሆሳዕና ቁጥራቸው የበዛ ሕጻናት አመሰገኑት፤ እሊህም ሕጻናት ከእናታቸው ጀርባ ያልወረዱ ነበሩ፡፡ ሕጻናት ከእናታቸው ጀርባ ወርደው አንደበት አውጥተው አመሰገኑት፡፡ የሕጻናት ምስጋና ሲደንቅ ድንጋዮች አንደበት አውጥተው አመሰገኑት፣ የሕጻናት እና የድንጋዮች ምስጋና ከመላእክት ምስጋና ጋር አንድ ኾነ እንደተባለ ሁሉ አንድ ኾነ፣ በአንድነት አመሰገኑት፡፡ ከዚህ በፊት ያልተደረገ፣ ከእንግዲህም በኋላም የማይደረግ እንደተባለ ሕጽናት ከእናታቸው ጀርባ እየወረዱ ያመሰገኑበት ከዚያ በኋላ አልተደረገም፣ ድንጋይም በሰው አንደበት ኾኖ ያመሰገነበት አልተደረገም ይላሉ የኔታ፡፡
ሁሉንም በትንቢት አስቀድሞ አናግሯል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሊቀ ካህናት እና በሽማግሌዎች ቢመሰገን ብዙ አይደንቅም፣ ሰይጣን የደነገጠ እና ያፈረው ሕጻናት ከእናታቸው ጀርባ ወርደው ሲያመሰግኑት ነው፣ አልፎም ድንጋይ ሲያመሰግን ደነገጠ አብዝቶም አፈረ ነው የሚሉት አበው፡፡ በድንጋይ መመስገን እንደ ምን ያለ ድንቅ ነው? በተናቀችው አህያ ጀርባ ላይ ኾኖ መምጣቱስ እንደ ምን ያለ ትሕትና ነው? እርሱ የሰላም አምላክ ነውና ለሰላም መጣ፣ እርሱ የትሕትና አምላክ ነውና ፍፁም ትሕትናውን በአህያ መጥቶ አሳየ፡፡ ትሑት ኾኖ ነው እንጂ ደመናዎች ይታዘዙለት፣ ጎዳናዎች ሁሉ ይጠቀለሉለት፣ ኑ ቢላቸውም ይመጡለት ነበርና፡፡
የኔታ እንደሚሉት እርሱ ትሑት ነውና ሲወለድ በበረት ተወለደ፤ አምላክ ኾኖ ሳለ ፍጡሩን አጥምቀኝ እያለ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ፤ ሰዎች በሚንቋት አህያ ላይ ተቀምጦ ሄደ፣ በጸሎተ ሐሙስም ዝቅ ብሎ እግር አጥቦ ፍጹም ትሕትናውን ገለጠ፡፡ በዓለ ሆሳዕናም የትሕትና፣ የሰላም በዓል ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ትሕትናውን በንግግር ሳይኾን በተግባር ደግሞ ደጋግሞ አሳየ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት በዐቢይ ጾም ጽናጽን አይጸነጸንም፣ ከበሮ አይመታም፣ ወረብ አይወረብም፣ ጭብጨባ አይጨበጨብም፣ በበዓለ ሆሳዕና ግን ከበሮ ይመታል፤ ጽናጽን ይጸነጸናል፤ ለአምላክ የሚቀርበው እልልታ ከዳር ዳር ያስተጋባል፤ ይሄም የኾነው ሆሳዕና የምስጋና ቀን ስለኾነች ምስጋና የሚቀርበው ከበሮ እየተመታ፣ ጽናጽን እየተጸነጸነ ነውና ይላሉ፡፡
ድንጋይ ባመሰገነበት ቀን ስለ ምን ከበሮ አይመታም? ሕጻናት ከእናታቸው ጀርባ ወርደው ባመሰገኑበት ቀን ስለ ምን ምስጋና አይቀርብም? ይህ እኮ ድንቅ ነገር ይላሉ የኔታ፡፡ ስርዓቷን ሰርታ የፈጸመችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም በስርዓቱ መሠረት በዓለ ሆሳዕናን በምስጋና ታከብራለች ነው የሚሉት፡፡ በበዓለ ሆሳዕና ምዕምናን ዘንባባ ይይዛሉ፤ ይህም የድል፣ የደስታ ምልክት ይላሉ የኔታ፡፡ ዘንባባውን ጨብጠውም በእልልታ ለአምላካቸው ምስጋና ያቀርባሉ፡፡ ሊቃውንቱም ያማረውን ባማረው ዝማሬ ያመሰግናሉ፡፡ ከሆሳዕና በኋላም ክርስቲያኖች ጫማቸውን ከእግራቸው ላይ አውልቀው፣ ስጋቸውን በጾም ቀጥተው፣ በስግደት አድክመው የጌታቸውን ሕማማት ያስባሉ፣ ሰሞነ ሕማማትንም በስርዓቱ ያከብራሉ፡፡
በዓለ ሆሳዕና የሰላም በዓል ነው፣ አምላክም የሰላም አምላክ ነው፣ የሰው ልጅ ከሰላም የበለጠ ነገር ይኖራል ብሎ ማሰብ አላዋቂነት ነው፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሚጎዱት ሰው በሠራው ነገር ነው፣ አምላክማ የመሬት መንቀጥቀጥ አያመጣብንም፣ የእሳተ ገሞራም አያስነሳብንም፣ ሰላም ብርጭቆ፣ ሰላም ብርሌ ናት፣ ሁልጊዜ የሚንከባከቧት፣ በጥንቃቄ የሚይዟት፣ ከእጅ እንዳታመልጥ የሚጠብቋት ይላሉ የኔታ፡፡
ሁሉም ሰላምን እንደ ብርጭቆና ብርሌ ሊጠብቃት ይገባዋል፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ሰላምን ይሻሉ፤ ሁሉም ወደ ኢትዮጵያዊነት ተመልሶ ሰላም ይጠብቃት ዘንድ ግድ ይለዋል፤ እልህና ቁጣ አይረቡም፣ ስክነት እና ብልሃት ያስፈልጋሉ፤ በበዓለ ሆሳዕና ብቻ ሳይሆን በሁሉም በዓላት የሰላም አዋጅ ነጋሪ ናቸው፣ የሰላም አዋጅ በሚነገሩባቸው በዓላት መጥፎ ነገር ልንሳማ አንፈልግም ነው የሚሉት፡፡
እንደ ሰው ዓለምአቀፋዊነት፣ እንደ ሃይማኖት ሰማያዊነት፣ እንደ ዜግነት ኢትዮጵያዊነትን አስቀድመን ሰላምን ልንጠብቅ ይገባል፤ ከዚህ ያነሱ መኾን መዋረድ ነው፣ በተለይም መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ ስለ ዘር፣ ስለ ጎጥ የሚያስተምር ቢኖር የተዋረደ ነው፣ ይህስ ማስተማር ቀርቶ መጽሐፍ ቅዱስን ይይዝ ዘንድ አይገባውም ይላሉ፡፡ ትሕትና በተደረገበት ቀን ትሕትናን አድርጉ፣ ሰላም በታወጀበት ቀንም ሰላምን አውጁ፡፡፡ እርሱ የትሕትና አምላክ ነውና፡፡
ምድር ደስታ ይብዛላት፤ ሰላም ይምጣላት፤ ሰቆቃና መከራ ይራቅላት፤ ወንድም ከወንድሙ ጋር ያዋደድባት፣ ጥላቻና ጥል ተነቅሎ ይጣልላት፤ በሆሳዕና እንደኾነው ሁሉ እልልታ ይሰማባት፤ ምስጋና ይበርክትባት፤ ውዳሴ ከዳር ዳር ያስተጋባባት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!