
የመጀመሪያው አዳሪ ትምህርት ቤት
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አዳሪ ትምህርት ቤት “መማር ሀገር ይለውጣል” በሚል መርሕ አልጋ ወራሽ ልዑል ተፈሪ መኮንን መከፈት እንዳለበት ከውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡ አልጋ ወራሹም በግል ገንዘባቸው ያሰቡትን ትምህርት ቤት አሰሩ፡፡ ስሙም “ተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት” ተባለ፡፡
አልጋ ወራሹ ትምህርት ቤቱን መርቀው ሲከፍቱ ለመሳፍንቱ እና ለመኳንንቱ ስለትምህርት መስፋፋት ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ በአረመኔዎች ብትከበብም ነጻነቷን ታግላ የጠበቀች የታሪክ ሀገር ነች ብለዋል፡፡
ይሁንና የዘመኑን ሥልጣኔ ለመያዝ እና እንደሌሎቹ ሀገራት የሕዝቦቿ ሕይወት የተሻለ ብርሃን እንዲያገኝ ለማድረግ እጅግ አድካሚ ጉዞና ተጋድሎ ይጠብቃታል ብለውም ነበር።
ስለ ሀገሩ ሲጠየቅ “ሀገሬን እወዳለሁ” የማይል የለም። ኾኖም ሀገሬን እወዳለሁ ማለት ብቻ በቂ አይደለም። በችግር ጊዜ ፈጥኖ ለመድረስ ካልኾነ ፍሬ አይኖረውም፤ ለዚህ ደግሞ ትምህርት ወሳኝ ሚና አለው ማለታቸው ይጠቀስላቸዋል፡፡
አልጋ ወራሹ አያይዘውም በዚያን ዘመን ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ መሠረት የኾነውን ዘመናዊ ትምህርት ልጆቿን ለማስተማር አቅም ስላጠራት ሀገራቸውን እንወዳለን የሚሉ ሁሉ የሀገር ፍቅራቸውን መግለጥ የሚችሉት ለተማሪ ቤቶች ማስፋፊያ እርዳታ ሲሰጡ እና ልጆቻቸውንም እንዲማሩ ሲያተጉ ነው ብለዋል፡፡
ያም ተባለ ይህ እሳቸው አዳሪ ትምህርት ቤቱን አስገንብተዋል፡፡ የተገነባው ይህ አዳሪ ትምህርት ቤትም ለተማሪዎች ምቹ ይኾን ዘንድ ከአውሮፓ የተገዙ የትምህርት መሳሪያዎች መሟላታቸውም ተነግሯል፡፡
በወቅቱ ልጁን ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ማስገባት የሚፈልግ ሰው ደግሞ ትምህርት ቤቱ ድረስ በአካል በመድሄድ ፈቃድ መጠየቂያ ወረቀት ላይ ሙሉ ስሙን፣ ሥራውን፣ መኖሪያውን እና የልጁን ስም መሙላት ግድ ይለዋል፡፡ በተጨማሪም ልጁ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ነዋሪ ኾኖ ወይም እየተመላለሰ እንዲማር ስለመፈለጉ ግዴታ ይገባል፡፡
ትምህርት ቤቱ በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ስሙን “ቪክቶር አማኑኤል” በሚል እንዲቀየር ተደረገ፤ የኢጣልያ ባለሥልጣናት ልጆች መማሪያም ኾነ፡፡ ከወረራው በፊት የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የነበሩት አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስግዶም ባካሄዱት መራር ትግል 2 ሺህ ያህል ተማሪዎች በአርበኝነት በመሳተፍ መስዋዕትነት ከፍለዋል።
በዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት የፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ ተስፋዬ ገሠሠ፣ መንግሥቱ ንዋይ፣ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር እና ሌሎችም ስመ ጥር ኢትዮጵያውያን ተምረውበታል፡፡
ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የኾነው አዳሪ ትምህርት ቤት የተከፈተው ሚያዝያ 19 ቀን 1917 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍን በምንጭነት ተጠቅመናል፡፡
————/////————/////———/////—–
“አቻ ያልተገኘለት የቴያትር ሰው”
ዊልያም ሼክስፒር በዓለም ካሉት ጸሐፊ ተውኔቶች ተወዳዳሪ ያልተገኘለት እንደኾነ ይነገራል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ብዙዎች በዘመናት ሁሉ አቻ ያልተገኘለት የቴያትር ሰው እንደኾነ አድርገው ይገልጹታል። ቴያትሮቹ እና ድርሰቶቹ ከ70 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉመው በብዙ ሀገራት እየታዩ ይገኛሉ፡፡
ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ በዓለም በርካታ ልብወለዶችን፣ ቴያትሮችን እና ግጥሞችን የጻፈው ሼክስፒር መኾኑን አስረግጦ አትቷል፡፡
ሰር ጆን የተባሉ ጸሐፊ በ1860 “ሜዲካል ኖውሌጅ ኦቭ ሼክስፒር” በተባለው መጽሐፋቸው ሼክስፒር የነበረው የሕክምና ዕውቀት በጣም የጠለቀ እንደኾነ አመልክተዋል። ደራሲ ጆን ሚቸልም በሼክስፒር ታሪክ ላይ ጥናት ያደረጉ ሲኾን “ሁሉን አወቅ የኾነው ደራሲ” ብለውታል።
የሼክስፔር የመጀመሪያ የግጥም መድበል “ቬኒስ እና አዶኒስ” ይሰኛል፡፡ በ1588 ደግሞ “ሮሚዎና እና ዡሊየት” የተሰኘው እስካሁን ድረስ ከፍተኛ አድደናቆት ያተረፈለትን ተውኔት ለመድረክ አብቅቷል፡፡
በ1589 ደግሞ ሄነሪ አራተኛ እና ሄኔሪ አምስተኛ የተሰኙትን ተከታታይ ድራማዎች ለመድረክ ካበቃ በኋላ በሃብት የደረጀ ኾኗል፡፡ ሐምሌት የተሰኘውን ቀዳሚው የትራጄዲ ተውኔቱ ለሕዝብ እይታ አብቅቷል፡፡ እያደርም የግሎብ ቲያትር ባለድርሻ ለመኾን በቃ፤ የእጹብ ድንቅ ቤት ባለቤትም ኾነ፡፡
ሼክስፔር በቀዳማዊት ንግስት ኤልሳቤጥ ጥያቄ ሜሪ ዋይፍስ ኦፍ ዊንደስርን ፅፏል፡፡ ቀጥሎም እንደ “ኦቴሎ ኪንግ-ሊር ፣ ማክቤዝ” የተሰኙትን ተውኔቶች ጽፎ ለሕዝብ ለእይታ በቅተዋል፡፡
ሼክስፔር በጸሐፌ ተውኔትነት ብቻ ሳይኾን በተዋናይነትም እየሠራ ሙያውን አበልፅጎታል፡፡
በስምንት ዓመት የምትበልጠውን ሄዛዊይንን በ18 ዓመቱ አግብቶ የሦስት ልጆች አባትም ነበር፡፡ የጸሐፊ ተውኔትነቱን ሥራ መተዳደሪያው ከማድረጉ በፊት በአስተማሪነት እና በወታደርነት እየተዘዋወረ ድራማ ከሚሠሩ ቡድኖች ጋር የዜግነት ግዴታን ተወጥቷል፡፡
ሼክስፒር ስትራትፎርድ-አፖን-አቮን በተባለ ሥፍራ በ1564 ተወልደ፡፡ በስትራትፎርድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን እንደተከታተለ ይነገራል፡፡ የግሪክ፣ የፈረንሳይ፣ የኢጣሊያ እና የስፔይን ቋንቋዎች ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነበር።
በተወለደበት ቀን ሚያዚያ 15 ቀን በ1616 ዓ.ም በ52 ዓመቱ በመኖሪያ ስፍራው ፎርድ አረፈ፡፡ ይህ በዓለም የሥነ ጽሑፍ ታሪክ አቻ ያልተገኘለት የቴያትር ሰው የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዳልተደረገለት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
———////———////———/////——-///////
የቴሌግራፍ “አባት”
የቴሌግራፍ ቴክኖሎጂን የፈለሰፈው ሳሙኤል ሞርስ በአሜሪካ ማሳቹሴትስ ከተማ የተወለደው በዚህ ሳምንት ሚያዝያ 19/1783 ነበር፡፡
ብላቴናው ሞርስ ያደገው በድህነት ቢኾንም ተግባቢ እና ጠያቂ ነበር፡፡ እያደርም የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ እና የስዕል ዝንባሌው ብሎም ችሎታው እደግ ተመንደግ የሚያስብለው ነበር፡፡ በመኾኑም ይዞታውን የተመለከቱ ጎረቤቶቹ ታዳጊው ወደ ታዋቂ የግል ትምህርት ቤት እንዲገባ እና በነጻ እንዲማር አደረጉ፡፡
በተለይ የሙያ ትምህርት አቀባበሉ ልዩ እንደነበር ሂስትሪ ዶት ኮም ዘግቧል፡፡ ሳሙኤል በኮሌጅ ቆይታውም ሒሳብ፣ ኤሌክትሪክ እና ፍልስፍና አጥንቶ ከዩኒቨርሲቲ በክብር ተመርቋል።
በመስከረም 1829 ሳሙኤል ሞርስ የሙከራ ቴሌግራፍ መሳሪያዎችን አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ማሽኑ የመጀመሪያውን መልዕክት ቢያስተላልፍም ጽሑፉ ግን ሊነበብ አልቻለም፡፡
ሳሙኤል ሞርስም “እንዴት?” በማለት ምርምሩን ቀጠለ፤ ለተከታታይ ስድስት ወራትም በቴሌግራፍ የተጻፈውን ጽሑፉ ሊነበብ እንዴት እንደሚችል ተደጋጋሚ ሙከራ በማድረግ ተሳክቶለታል፡፡
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1844 ለሞርስ ጥንካሬ ምስጋና ይግባውና በዋሽንግተን እና በባልቲሞር መካከል የቴሌግራፍ መስመር ተዘረጋ።
በተከፈተበት ቀንም “ጌታ ሆይ፣ ሥራህ ድንቅ ነው!” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐረግ ሞርስ ላከውና ተሳካለት።
ሳሙኤል ሞርስ ከሥነ ሥዕል እና ከቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራው ባሻገር እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ለትምህርት ቤቶች፣ ለዩኒቨርሲቲዎች እና ለቤተ-ክርስቲያናት በማበርከት አንቱታን አትርፏል፡፡ ልበ ብርሃኑ ሞርስ ሚያዝያ 2 ቀን 1872 ከዚህ ዓለም ተለየ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!