
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት “ሴቶች እና አመራር” በሚል መሪ መልዕክት ለሴት መሪዎች እና ባለሙያዎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ ሥልጠናው የሴቶችን የፖለቲካ ታሳትፎ፣ የአመራር ክህሎት እና ውሳኔ ሰጭነት አቅም ለማሳደግና ለውጥ ለማምጣት ዓላማ ያደረገ ነው፡፡
በሥልጠናው እየተሳተፉ የሚገኙት አዲሴ ንጉሤ “ያለ ሴቶች ተሳትፎ ግብ የሚመታ ዓላማ የለም” ብለዋል፡፡ ሴቶች የኅብረሰተቡ ግማሽ አካል ነን ያሉት ወይዘሮ አዲሴ ሴቶች ያልተሳተፉበት ሥራ ውጤታማ ሊኾን አይችልም ብለዋል፡፡ መሪነትን ለማጎልበት እና ብቁ ለማድረግ የሚሠጠው ሥልጠና ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
ሴቶች በመሪነት ደረጃ ብቁ ከኾኑ የሚፈለጉ ዓላማዎችን ለማሳካት ምቹ እንደሚኾንም ገልጸዋል፡፡ የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል የኾኑትን ሴቶች አቅም ሳይገነቡ ሀገርን ወደሚፈለገው ደረጃ ከፍ ማድረግ አይቻልም ነው ያሉት፡፡ የሚፈለገውን ግብ ለማሳካት የሴቶችን አቅም ማጎልበት ግዴታ ነው ብለዋል፡፡
ሴቶች የሚሰጣቸውን ኀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ አቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች ደግሞ የበለጠ ለመሥራት ይረዳሉ ነው ያሉት፡፡ ከሥልጠናው የሚያገኙትን ግብዓት ወደ ተግባር ለመቀየር ቁርጠኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ሁሉም በቁርጠኝነት ከሠራ ግቡን ማሳካት ይቻላልም ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ወደዘላቂ ሰላም ለመለወጥ የሴቶች ሚና ላቅ ያለ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ሰላምን ለማምጣት ሁሉም ሰው ራሱን ሰላማዊ ማድረግ እና ስለ ሰላም መስበክ እንደሚገባው ነው የተናገሩት፡፡ ከቀውስና ከግጭት ውስጥ መቆየት ይበቃናል ብሎ መውጣት ይገባልም ብለዋል፡፡
ሌላኛዋ በሥልጠናው የተሳተፉት አስማረች ምስክር ለሴቶች የሚሰጡ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ሴቶች ለሀገር ግንባታ ያለንን አስተዋጽኦ ከፍ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡ የሀገር ግንባታን ከፍ ለማድረግ ሴቶችን ማብቃት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ሥልጠናው ጉድለቶችን የለየ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሴቶችን ወደ መሪነት ለማምጣት እና ውሳኔ ሰጭነታቸውን ለማሳደግ ወሳኝ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ችግር ሲፈጠር ቅድሚያ የችግር ተጋላጮች ሴቶች ናቸው ያሉት ሠልጣኟ ከችግሩ ለመሻገር የሴቶች ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ መፍትሔዎችን ለማመንጨት እና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሴቶች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው ዕውቀትን እና የአመራር ክህሎትን እንደሚያዳብር ተናግረዋል፡፡ ለሴቶች የሚሰጠው አቅምን የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የአማራ ሥራ አመራር ኢኒስትቲዩት አማካሪ ይትባረክ አወቀ ክልሉ በውስጥም በውጭም የሰላም እጦት እንደገጠመው ተናግረዋል። የክልሉ የሰላም እጦት በአንድም በሌላ በመንገድ ከአመራር መጓደል ጋር እንደሚመጣ ጠቁመዋል። ሴት መሪዎችን እያበቁ፣ እየገነቡ እና በተግባር እያሳተፉ በመሄድ በኩልም መሠረታዊ ችግር መኖሩን ነው የተናገሩት።
ከተለመደው የፖለቲካ ባሕል አኳያ ሴቶችን የማሳተፍ እና የመሪነት ሚና አምኖ ተቀብሎ በመስጠት ረገድ ጉድለቶች አሉ ነው ያሉት። መሠረታዊ ጉድለቶችን አርሞ መሄድ እንደሚገባም አመላክተዋል። ሴቶች ያልተሳተፉበት ሁሉም ነገር ውጤታማ እንደማይኾን እና ዳር እንደማይደርስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረዳን መጥተናል ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የሴቶች አቅም ለክልሉ ሁለንተናዊ እድገት የሚኖረውን ሚና በመረዳት ሥልጠና ለመስጠት ማመቻቸታቸውን ነው የተናገሩት። ሠልጣኝ ሴቶች ሌሎች ሴቶች ለላቀ ልማት፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እንዲበቁ የማድረግ ኀላፊነት አለባቸው ነው ያሉት። ሴቶች ለሰላም ያላቸውን ቅርበት፣ ለሰላም የሚያወጡትን ከፍተኛ ዋጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ማንኛውም የሃሳብ ልዩነት በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ለማድረግ አቋምና ብቃት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሥልጠና እንደሚሠጥም ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ውስጥ ማንኛውም ልዩነት በመሣሪያ ሳይኾን በሃሳብ አሸናፊነት የሚፈታበተን ትክክለኛ አካሄድ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት። ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት አውድን ለመፍጠር የሴቶች ሚና ከፍ ያለ መኾኑንም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምኅረቴ ዋለ ኢንስቲትዩቱ የክልሉ የማስፈጽም አቅም መገንቢያ ማዕከል፣ ለውጥ አስቀጣይ ተቋም፣ የክልሉ የሃሳብ መፍለቂያ ተቋም ለመኾን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ የማስፈጸም አቅምን ለመገንባት የሰው ኃይልን ማብቃት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የሴቶችን የአመራር እና የውሳኔ ሰጭነት ብቃት ከፍ ለማድረግ ሥልጠና ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ የሴቶችን ፖለቲካዊ ብቃት ለማሳደግ ብቁ በኾኑ አሠልጣኞች ሥልጠና እየሠጡ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ቀውስን ለመቋቋም ብቃት እና አመለካከት ያስፈልጋል ያሉት ኀላፊው ሥልጠናው የሴቶችን ብቃት እና ውሳኔ ሰጭነት ለማሳደግ እንደሚረዳ ይታመናል ነው ያሉት፡፡
በአመራር ሥርዓቱ ያለውን ችግር ለመፍታት ኢንስቲትዩቱ በምርምር የታገዘ ሥራ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ መሪዎችን ለማብቃት የሚያስችል ሥርዓት እየተዘጋጀ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የአመራር ክፍተቶችን በምርምር በመታገዝ ለማረም እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!