“ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ እየሠራን ነው” የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

28

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አስቸኳይ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ.ር) ገለጹ። ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ.ር) በተለያዩ አካባቢዎች በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እየቀረበ መኾኑንም ገልጸዋል።

የሰብአዊ ድጋፉ በየሩብ ዓመቱ እንደሚሰራጭ ጠቅሰው ከጥር እስከ መጋቢት ድረስ ለ6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል። አሁን ባለንበት ወቅትም ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ የማድረጉ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ድጋፉ በመንግሥትና በአጋር አካላት ትብብር እንደሚከናወንም እንዲሁ።

በአጠቃላይ ከሚያዚያ እስከ ሰኔ ላለው ድጋፍ 11 ቢሊዮን ብር አካባቢ ወጭ የሚጠይቅ ሲሆን 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ድጋፍ በመንግሥት ይሸፈናል ነው ያሉት፡፡ ቀሪው በለጋሽ አካላት እንደሚሸፈንም ነው የተናገሩት፡፡

ኢዜአ እንደዘገበው የመንግሥት ዋነኛ ትኩረት አደጋን ቀድሞ መከላከል መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ለዚህም የተጋላጭነት ልየታ የአደጋ ስጋት ፕሮፋይል ጥናት መሠራቱን ጠቁመዋል። በሀገሪቱ ከሚገኙ ወረዳዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በዚህ ጥናት መሸፈናቸውንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሲዳማ ሕዝብ ዘመን መለወጫ በአል “ፊቼ ጫምባላላ” በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው።
Next article“ሥልጠናው የሴቶችን የመሪነት ብቃት እና ውሳኔ ሰጭነት ለማሳደግ የሚያግዝ ነው” የክልሉ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምኅረቴ ዋለ