
አዲስ አበባ፡ ሚያዝያ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገራዊ ምክክሩ የሴቶች ተሳትፎና ሚና ላይ ያተኮረ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡
ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር በርካታ ሀገራት ግጭቶች እና ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን በምክክር ፈትተዋል ብለዋል። እኛም ይህን ልምድ ተግበራዊ በማድረግ የሀሳብ ልዩነቶችን በምክክር መፍታት አለብን ነው ያሉት።
በሀገሪቱ የቆዩ እና ስር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታት ከምክክር ውጭ አማራጭ ያለ አይመስለኝም ነው ያሉት። በማንኛውም ሀገራዊ እና ሕዝባዊ ጉዳይ ላይ የሴቶች ተሳተፎ ግድ መሆን አለበት ያሉት ፕሬዝዳንት ሳኅለወርቅ በሀገሪቱ በሚካሄደው ሀገራዊ ምክክርም ሴቶችን ማሳተፍ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው በብሔራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሴቶች ከኮታ እና ቁጥር የዘለለ ውክልና እንዲኖራቸው እንሻለን ብለዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ ጨምረውም የሴቶች ተሳትፎ ሙሉና ትርጉም ያለው እንዲኾን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ሴቶች በተሳታፊዎች ልየታ እና በተወካዮች መረጣ ሂደትም ቢያንስ 30 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው አሠራር እንደተዘረጋም አብራርተዋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) በበኩላቸው ሴቶች የምክር እና የምክክር ጥበብ ያላቸው በመኾኑ ዘላቂ ሰላም እና የሀገር እድገትን ለማምጣት ይህን ወሳኝ አስተዋጾቸውን መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!