ባለፈው ዓመት አርሶ አደሩን ቅሬታ ውስጥ የከተተው የግብዓት እጥረት እንዳይደገም እየተሠራ መኾኑን የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ፡፡

20

ደብረ ማርቆስ፡ ሚያዝያ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን የሥራ ኃላፊዎች የዞኑን ያለፉት 9 ወራት የልማት፣ የሕግ ማስከበር እና የሰላም ግንባታ ሥራዎች ሲገመግሙ በትኩረት ከተመለከቷቸው ዘርፎች መካከል የግብርና ተግባራት ይገኙበታል፡፡

ባለፉት ጊዜያት በዞኑ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ በግብርና እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል ያሉት የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ፍሬው ካሴ ናቸው፡፡በዞኑ ሕግን ከማስከበር ጎን ለጎን የታቀደውን ማሳካት ባይቻልም የተለያዩ የግብርና ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ብለዋል፡፡

በ2016/17 የመኸር ምርት ዘመን ከ6መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን መታቀዱን የዞኑ ግብርና መምሪያ መረጃ ያመላክታል፡፡ታዲያ ይህን ለማሳካት የግብዓት አቅርቦት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ባለፈው ዓመት አርሶ አደሩን ቅሬታ ውስጥ የከተተው የግብዓት አቅርቦት እጥረት በዚህ ዓመት እንዳይደገም ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ምክትል መምሪያ ኃላፊው ለዞኑ ከተመደበው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን ከ350 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆውን ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የአመራር ቁርጠኘነት እና መናበብ በዚህ ጊዜ ትልቅ ሚና ይጫወታል ያሉት የሥራ ኃላፊዎች ባላፉት ጊዜያት የዞኑን ሰላም ለማሻሻል እና የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለመፈጸም በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ቢሆን ሰፊ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በዞኑ ያጋጠመው የሰላም እጦት በኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማት ዘርፎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ነው የገለጹት፡፡ የግብርናው ዘርፍም ቀደሚ ተጎጅ መሆኑን አመላክተዋል፡፡በዞኑ አሁን ላይ እየታየ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ በማድረግ የልማት እና ሰላም ግንባታ ተግባራትን በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአዲስ አበባ የላቀች የዲፕሎማሲ ማእከል ሆና እንድትቀጥል መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ።
Next articleበምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ የተመራ የከፍተኛ መሪዎች ልዑክ የልማት ሥራዎችን ለመመልከት ኮምቦልቻ ገባ።