
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ መዲናችን የላቀች የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና እንድትቀጥል አደራ መወጣታችን የሁልጊዜ ተግባር ሊሆን ብለዋል። ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ እና 44ኛው የአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈፃሚዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና እና እውቅና በሰጠበት መርሐግብር ላይ ነው።
የእውቅና እና የምሥጋና አሰጣጥ መርሃ ግብሩ ዝግጅት በብሔራዊ ኮሚቴ አማካኝነት መከናወኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ለሀገራችን የተሰጠውን ታሪካዊ ኃላፊነት እና ክብር በሚመጥን አኳኋን በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ያደረጉ አካላትን አመሥግነዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ መስተንግዶ በስኬት በማዘጋጀት ያዳበርነውን ባሕላችንን አጠናክረን መቀጠል ብቻ ሳይሆን መዲናችን የላቀች የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና እንድትቀጥል አደራ መወጣታችን የሁልጊዜ ተግባር ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
ኢዜአ እንደዘገበው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና የብሔራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በጉባኤው የተሳተፉ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እንግዶችን በተሳካ መልኩ ተቀብሎ በመሸኘት እንዲሁም የተሟላ አገልግሎት ለሰጡ ተቋማት ምሥጋና አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!