
ደሴ: ሚያዝያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገ የግል ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ለ20 ዓመታት ያክል በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ አቅም የሌላቸው እና ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የድርጅቱ የትኩረት ዘርፎች ሲኾኑ ለእነዚህ አካላት ተንቀሳቃሽ ነጻ የላብራቶሪ አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡
የኢንተርናሽናል ክሊኒካል ላብራቶሪ የፕሮጀክት ዳይሬክተር ክፍሌ ጥላሁን (ዶ.ር) አሁን ላይ ለተጎዱ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሲቢሲ እና የኬሚስትሪ ናሙናዎችን በመውሰድ በደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነጻ የተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ አገልግሎት እየሰጡ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡
የደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ሃይማኖት አየለ (ዶ.ር) ነጻ የተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ አገልግሎት በነጻ መሰጠቱ ለደሴ እና አካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡ በሆስፒታሉ ላብራቶሪ ክፍል ያለውን ጫናም የሚያቃልል መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ሥራ አሥኪያጁ የተንቀሳቃሽ ነጻ ላብራቶሪ አገልግሎት በሆስፒታሉ ለሦስት ወራት እየተሰጠ እንደሚቆይም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፊኒክስ ሐየሎም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!