“የዓለም ስጋት” አባ ሰንጋ (አንትራክስ)!

78

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሰዎች፣ በእንስሳት ወይንም በአዝዕርት ላይ ጉዳት ለማድረስ በዓለም ላይ ቫይረስ፣ ባክቴሪያ ወይንም ሌሎች ጀርሞችን መልቀቅ ነው “ባዮቴሬሪዝም”። ከዚህ ውስጥ ደግሞ የአንትራክስ በሽታ አምጭ የኾነው “ባሲለስ አንትራሲስ” የተባለው ባክቴሪያ ዋነኛ ባዮሎጅካል የጦር መሳሪ ተደርጎ ተቀምጧል።

የዓለም ጤና ድርጅትም “የዓለም ስጋት” ብሎ ከለያቸው ከእንስሳት ወደ ሰው ከሚተላለፉ በሽታዎች ውስጥ አባሰንጋ (አንትራክስ) አንዱ አድርጎ አስቀምጦታል። ባክቴሪያው ከ50 ዓመት በላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ በአፈር ውስጥ መኖር ይችላል። ምቹ ሁኔታ ሲያገኝ ደግሞ አንሰራርቶ ወደ እንስሳት በመግባት ጉዳት ማድረስ ይችላል። በበሽታው የተጠቁ እንስሳት ተዋጽኦን መመገብ ደግሞ ባክቴሪያው ወደ ሰው እንዲተላለፍ ምክንያት ይኾናል።

ባክቴሪያው ከአንታርክቲካ አህጉር ውጭ በየትኛውም ዓለም ተሰራጭቶ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአንድ ጤና ምልከታ ፎካል ሀብታሙ አለባቸው ነግረውናል። ባክቴሪያው ለአጥፍቶ መጥፋት ተግባር ሊውል ይችላል ተብሎ ከሚታሰቡ ባዮሎጅካል የጦር መሳሪያዎች አንዱ ነው። “እጅግ ገዳይ” ከሚባሉት ውስጥም እንደሚጠቀስ አንስተዋል። አንድ የአባ ሰንጋ ተጠቂ ከተገኘ ወዲያውኑ ወይንም በ30 ደቂቃ ውስጥ ሪፖርት ከሚደረጉ በሽታዎች መካከል አንዱ ኾኖ ተቀምጧል።

በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ ኾኖ ቢቀመጥም እንደ ኢትዮጵያ መሠረታቸውን ግብርና ላይ ያደረጉ እና ከቤት እንስሳት ጋር ቁርኝታቸው ቀጥተኛ በኾኑ ሀገራት እየሰፋ መምጣቱን ባለሙያው ገልጸዋል። በአማራ ክልልም በ2016 በጀት ዓመት ከ900 በላይ የአባ ሰንጋ ሕሙማን እና የሁለት ሰዎች ሞት ተመዝግቧል። ከዚህ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚኾነው ሕሙማን በሰሜን፣ ማዕከላዊ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች እና ዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተመዘገበ እንደኾነ ነው የጠቀሱት። ከክልሉ 83 በመቶ የሚኾነው ችግር ደግሞ በሰሜን ጎንደር ዞን እና ዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተከሰተ ነው።

በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ለተጠቂዎች ቁጥር ማደግ እንደ ምክንያት ሊነሳ እንደሚችል አንስተዋል። በሽታውን ለመከላከል በክልሉ የእንስሳት ክትባት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። ከክትባት ባለፈ በበሽታው ሕይወታቸው ያለፈ እንስሳት ካጋጠመ በአግባቡ እንዲወገዱ ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በበሽታው የተጠቁ ሰዎችንም ሕክምና እየተሰጠ መኾኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ሥራቸው ከቆዳ ምርት፣ ስጋ ቤቶች እና ከመሳሰሉ ለችግር ይበልጥ ተጋላጭ በኾኑ ሥራዎች ለተሰማሩ ሰዎች ክትባት ለመስጠት መታቀዱን ገልጸዋል። የበሽታውን አስከፊነት አስመልክቶ ለማኅበረሰቡ የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተጠናክሮ ይቀጥላል። በክልሉ በባሕር ዳር እና ደሴ ላይ አባሰንጋን ለመመርመር የሚያስችል የምርመራ ቦታዎችን ለማቋቋም እየተሠራ ይገኛል።

ማኅበረሰቡ ምርመራ ያልተደረገለትን የእንስሳት ስጋን ተከፋፍሎ ከመመገብ እንዲቆጠብ አሳስበዋል። በሽታውን ለመከላከል ማኅበረሰቡ የሚሰጡ ትምህርቶችን ተቀብሎ እንዲተገብርም ተጠይቋል። እንስሳትን ማስከተብ፣ የሞቱ እንስሳትን ደግሞ ከጤና ባለሙያ ጋር በመመካከር በአግባቡ የማስወገድ ሥራ መሥራት ይገባልም ብለዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት እና አጋር አካላት ደግሞ በበጀት እና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ሥራውን በትኩረት እንዲሠሩ ጠይቀዋል። ሕግ አውጭው አካል እንስሳትን ማስከተብ የሚያስችል አስገዳጅ መመሪያዎችን በማውጣት ተግባራዊ ማድረግ ይገባዋልም ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleስኬታማ የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማስቀጠል ክልሎች የእርስ በእርስ የፓለቲካ ሥራ ግንኙነታቸውን ማጠናከር አለባቸው ተባለ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማርክ ሱዝማን እና ቡድናቸውን ተቀበሉ።