
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና የአቅም ግንባታ ዘርፍ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአሶሳ ከተማ መካሄድ ጀምሯል። በግምገማ መድረኩ የሁሉም ክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አሥተዳደር የዘርፉ ኀላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በመድረኩ የብልጽግና ፖርቲ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን የብልጽግና ፓርቲ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ሁለንተናዊ ለውጦችን እውን ማድረግ በሚያስችል መልኩ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ፓርቲው በአመለካከት እና በተግባር የተዋሀደ መሪን በመፍጠር ቅቡልነት ያለው የሀገረ መንግሥት ሥርዓት ለመገንባት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ የሕዝቡን ተሳትፎ፣ ተጠቃሚነት እና እርካታን ማረጋገጥ ዋና ዓላማው አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በፓርቲው በሁሉም ዘርፍ እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች አዎንታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውንም አስታውቀዋል።
የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በጥልቀት በመገምገም ለቀጣይ ሥራ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ የሚያስችል አቅጣጫ ማስቀመጥ የሚያግዝ መድረክ መኾኑን ጠቁመዋል። የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) መድረኩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዘርፉ ካስቀመጥነው ዕቅድ አኳያ አፈጻጸሙን በጋራ በመገምገም ያለንበትን ደረጃ ለመለየት እና በቀጣይ የተግባራትን ስኬታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ነው ብለዋል፡፡ ውጤታማ የክትትል እና የድጋፍ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።
ኀላፊው አያይዘውም ስኬታማ የፓለቲካ እና የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማስቀጠል ክልሎች የእርስ በእርስ የፓለቲካ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የግምገማ መድረኩ የ2017 ዓ.ም የዘርፉ የርብርብ ማዕከል ተለይቶ አቅጣጫ እንደሚቀመጥበትም ኀላፊው አስታውቀዋል።
ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው የግምገማ መድረኩ ሁሉም ክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አሥተዳደር የዘርፉ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የሚደረግ እና የቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት ወሳኝ መድረክ እንደኾነ ተገልጿል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!