
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በዚህ ዓመት እስካሁን 293 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ መልማቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል። ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ እንደ ሀገርም ኾነ በክልል ደረጃ ለመስኖ ልማቱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል።
በደቡብ ወሎ ዞን በቃሉ ወረዳ 01 ቀበሌ እና በሌሎቹም በመስኖ እየለማ ያለው የቲማቲም እንዲሁም የሽንኩርት ክላስተር ተጎብኝቷል፡፡
በጉብኝቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ(ዶ.ር)፣ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን፣ የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኛው እና ሌሎች የክልል እና የዞን የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ 333 ሺህ ሄክታር መሬት በዚህ ዓመት በመስኖ ለማልማት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ዶክተር ድረስ እስካሁን 293 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ የአትክልት፣ ፍራፍሬ እንዲሁም በሌሎች ማልማት እንደተቻለ ነው ያስረዱት፡፡
እየተካሄደ ያለው የልማት ሥራ በግብርና ምርት ፍላጎት እና አቅርቦት መካከል ያለውን አለመጣጣም ለማስተካከል እንደሚቻልም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ዶክተር ድረስ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ እና በሌሎችም አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የተመለከቱት የመስኖ ልማት የታቀደውን የምርት ግብ ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ እንደሚኾንም አመላክተዋል።
ለመጭው ክረምት ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የችግኝ ዝግጅትም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል። የቃሉ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሙህዲን አህመድ በወረዳው ከ3ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ መኾኑን ጠቅሰዋል።
እየተመረተ ባለው የቲማቲም እና የሽንኩርት ምርት በተሻለ ደረጃ ገበያውን የማረጋጋት ሥራ መሠራቱንም አብራርተዋል። በጉብኝቱ የክልሉ እና የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የበጋ አትክልት ችግኝ ተክለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!