የራያ አሁናዊ ሁኔታ እና የሰብዓዊ ድጋፍ

114

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 18/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሕወሓት ታጣቂዎች ለአራተኛ ጊዜ ባደረጉት ወረራ በሰሜን ወሎ ዞን በራያ ወረዳዎች በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የሕወሓት ታጣቂዎችም ቤት ንብረታቸውን እያወደሙ፣ እየዘረፉ መኾናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት ሕወሓት ያደረገውን ወረራ በተመለከተ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ “ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ መማር የተሳነው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈጽሟል” ብሏል፡፡

“የአማራ ክልል መንግሥት በተደጋጋሚ ከትግራይ ጊዜያዊ አሥተዳደር ጋር በፌዴራል መንግሥት አማካኝነት ውይይት ለማድረግ በርካታ ሙከራዎች የተደረጉ ቢኾንም ሕወሓት ይህን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም እና ዛታ አካባቢዎች ላይ ወረራ ፈጽሟል” ሲልም በመግለጫው አንስቷል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት “ይህን መሰሉን የሕወሓት እና የግብረ አበሮቹን ፖለቲካዊ ግልሙትና እና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማድረግ ከመሞከር እንዲታቀብና የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በማክበር በአጭር ጊዜ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ” ጠይቆ ነበር።
የሕወሓት ታጣቂዎች ግን በወረራ ከያዟቸው አካባቢዎች አልወጡም፡፡ ለደኅንነታቸው ስጋት ቀያቸውን ለቀው የወጡ ወገኖችም በመጠለያ ውስጥ ለመኖር ተገድደዋል፡፡

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን የተውናቸው ከራያ አላማጣ ወረዳ ተፈናቅለው በዋጃ ጊዜያዊ መጠያ ውስጥ የሚገኙ እናት የሕወሓት ታጣቂዎች ባደረጉት ወረራ እና ጥቃት ሸሽተው መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ የሕወሓት ታጣቂዎች በደረሱባቸው አካባቢዎች ሁሉ ሃብት ይዘርፋሉ፣ ያወድማሉ፣ ንጹሐንን ይጎዳሉ ነው ያሉት፡፡ በቤት ውስጥ ብቻ ሳይኾን በአትክልት እና ፍራፍሬ ላይም ውድመት እያደረሱ መኾናቸውን ነው የገለጹት፡፡

በቂ የኾነ መጠለያ እንደሌላቸውም ገልጸዋል፡፡ በመጠለያ ስጋት እንዳለባቸውም ተናግዋል፡፡ የእለት ምግብ ትሰጣላችሁ ብንባልም እስካሁን አልደረሰንም፤ የአካባቢው ማኅበረሰብ በሚሰጠን ድጋፍ ነው ያለነው ብለዋል፡፡ ሕጻናት እየተጎዱ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
“የምንፈልገው ሰላም ነው፣ በሰላም በቤት ተቀምጦ ጠዋት ተነስቶ ቤት ጠርጎ ቡና መጠጣትም ትልቅ ነገር ነው” ነው ያሉት፡፡

ከራያ ባላ ወረዳ የተፈናቀሉት አባት ደግሞ በሕወሓት ታጣቂዎች ወረራ የአካባቢው ማኅበረሰብ መፈናቀሉን ተናግረዋል፡፡ የሕወሓት ታጣቂዎች የሰላም ስምምነቱን በኃይል በመጣስ ከቀያችን አፈናቅለውናል፣ በማንነታችን ላይም መጥተውብናል ነው ያሉት፡፡ የዘር ወቅት በቀረበበት ጊዜ በመፈናቃላቸው ጉዳቱ ከፍ ያለ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

“የራያ ባላ ወረዳን ሕዝብ እያሰቃዩ፣ ንብረቱን እየዘረፉ፣ አፈናቅለው እነርሱ ይዘውታል፤ ገበሬውን አፈናቅለው አትክልቱን እየነቀሉት ነው፤ ንብረቱን አግዘው ወስደውታል” ነው ያሉት፡፡ ሕጻናት ተቸግረዋል፤ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል ብለዋል፡፡

እርዳታ ትሰጣላችሁ ተብለው እየተጠባበቁ መኾናቸውን እና እስካሁን የደረሳቸው ድጋፍ እንደሌለም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት አካባቢውን ሰላም አድርጎ እንዲመልሳቸውም ጠይቀዋል፡፡ “ሚያዝያ ነው፣ ዝናብ ጥሏል፤ የዘር ወቅት ነው፣ እርዳታው ቀርቶብን ወደቀያችን በመለሱን፣ መሬታችን ዘርተን ራሳችንን እንችል ነበር፣ በጣም ተቸግረን ነው ያለነው፣ መንግሥት ወራሪዎችን አባርሮ ማንነታችን እንዲያረጋገጥ እንፈልጋለን” ነው ያሉት፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አራጌ ይመር የወሰን እና የማንነት ጥያቄ ያሉባቸውን አካባቢዎች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በሰላማዊ እና በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት በሚደረግበት ወቅት የሕወሓት ወራሪ ኃይል ሰላማዊ አማራጮችን ትቶ ወረራ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ የሕወሓት ወራሪዎች በፈጸሙት ወረራ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች መፈናቃላቸውንም ተናግረዋል፡፡

የዞኑ አሥተዳደር ከወረዳ መሪዎች ጋር በመኾን የተፈናቀሉ ወገኖች የሚያርፉበትን ቦታ ከማመቻቸት ጀምሮ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በወረራው ምክንያት ከ39 ሺህ በላይ የተመዘገቡ ተፈናቃይ ወገኖች መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ይህ ቁጥር በራያ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ወገኖች መሆኑንም ጠቅሰዋል። ሌሎች ያልተመዘገቡ ሰዎች በግለሰቦች ቤት እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡

የእለት ምግብ ለማድረስ ለአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ጥያቄ በማቅረብ ድጋፉ እስኪመጣ ድረስ በራስ አቅም ድጋፍ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም የእለት ምግብ በማቅረብ ትልቅ ድጋፍ ማድረጉን ነው የተናገሩት፣ የራያ አላማጣ፣ የራያ ባላ ወረዳዎች እና የአላማጣ ከተማ አሥተዳደር ከራሳቸው በጀት ላይ ለተጎዱ ወገኖች የዕለት ድጋፍ እንዲደርስ ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ወገኖች የእለት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል አደጋ ስጋት ኮሚሽንም ድጋፍ ማድረጉን ያነሱት ዋና አሥተዳዳሪው ድጋፉ ሁሉንም ወገኖች የሚያዳርስ ባለመኾኑ ቅድሚያ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እየሰጡ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የሰባዓዊ መብት ተቋማት ወደ አካባቢው ሄደው ችግሩን ማየታቸውንም አንስተዋል፡፡

ከአላማጣ ከተማ አሥተዳደር የተፈናቀሉ ወገኖች ወደቀያቸው መመለሳቸውንም ገልጸዋል፤ ገጠር አካባቢዎች ላይ ባለው ሰፊ ወረራና ዘረፋ ምክንያት የራያ አላማጣ እና የራያ ባላ ወረዳ ነዋሪዎች በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ አካባቢው በተደጋጋሚ ወረራ የተፈጸመበት በመኾኑ በልማት እና በመልሶ ግንባታ ተጎድቶ መቆየቱንም አመላክተዋል፡፡ ተደጋጋሚ ጉዳት የደረሰበት አካባቢ በመኾኑ በመጠለያ ውስጥ ያሉ ብቻ ሳይኾን ወደ ቀያቸው የተመለሱ ወገኖችም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡

ዋናው መፍትሔ ለዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ ብቻ ሳይኾን የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ወደ ቀያቸው መመለስ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ወገኖችን ወደቀያቸው መመለስ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ ሕወሓት የወረረን የሰላም ስምምነቱን አፍርሶ መኾኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እያሳወቅን ነው ብለዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ተወካዮችም ሁለት ጊዜ መጥተው ማየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ሰላም ፈላጊዎች መኾናችን፣ እንዳልተነኮስን እና ሰላማዊ የኾኑ አማራጮችን እንደምንመረጥ ግልጽ አድርገናል፤ የአማራ ክልል መንግሥት ሕወሓት ከወረራቸው አካባቢዎች እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል፤ ነገር ግን እስካሁን አልወጡም ነው ያሉት፡፡

የሕወሓት ታጣቂዎች ሰላማዊ ጥሪዎችን አክብረው የሚወጡ ካልኾነ መንግሥት በሚያስቀምተው አቅጣጫ መሠረት ወረራውን ለመቀልበስ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡ በጦርነት የለማ ሀገር እና የተገነባ የሰው ኃይል የለም ያሉት አሥተዳዳሪው የሰላም ስምምነቱን ማፍረስ ለሌላ ግጭት እና ችግር እንደሚዳርግ ተናግረዋል፡፡ የሰላም ስምምነቱን ማፍረስ ካለፉት ስህተቶች አለመማር እና ከጦርነት የተረፈውን ሕዝብ ማስጨረስ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ሕወሓት የሰላም ስምምነቱን አፍርሶ ግጭትን ከመረጠ የሚጣላው ከአማራ ሕዝብ ጋር ብቻ ሳይኾን እንደለመደው ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር ነው ብለዋል፡፡ ቅድሚያ የተሰጠው በሰላማዊ መንገድ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ነው ያሉት አሥተዳዳሪው ለዘላቂ ሰላም ሲባል ሰላማዊ አማራጮችን መጠቀም ከፍርሃት መቁጠር እንደማይገባም አስገንዝበዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሕወሓት ያደረገው ወረራ ሕዝባችን ለዳግም ስቃይ እና ችግር እያደረገ መኾኑን ሊያውቁልን ይገባል ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በጎንደር ከተማ ውስጥ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍ ያለመ ምልከታ እያደረጉ ነው።
Next article“በአማራ ክልል እስካሁን 293 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለምቷል” ግብርና ቢሮ